ብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚታወቅባቸውን መልካም እሴቶች አጠናክሮ መቀጠል አለበት - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚታወቅባቸውን መልካም እሴቶች አጠናክሮ መቀጠል አለበት - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ)፦የአዊ ብሔረሰብ ዞን የሚታወቅባቸውን እሴቶችና መልካም ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
86ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል “የአብሮነት ቅርስ፤ የሰላም ውርስ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዊ ዞን እንጅባራ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
በዚሁ ጊዜ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት፣ የአገው ህዝብና ፈረስ ለዘመናት የዘለቀ ቁርኝት ያላቸው መሆኑን የአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓል ዝግጅት ማሳያ ነው ብለዋል።
የአገው ህዝብ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ የሚኖር፣ ለሰላም የላቀ ዋጋ የሚሰጥና በታታሪነቱ የሚታወቅ የዘርፈ ብዙ እሴት ባለቤት መሆኑን ተናግረዋል።
ዞኑ የሚታወቅባቸው እሴቶችና መልካም ተግባራት ተጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ጽንፈኝነትንና ጥላቻን በጽናት በመታገል ለሰላም መስፈን አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም በደምና አጥንቱ የኢትዮጵያን ታሪክ እንዳቆየ ሁሉ አሁን ደግሞ እውቀቱንና ጉልበቱን በመጠቀም የሀገሩን ብሎም የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የልማት አርበኛ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በበኩላቸው፤ የአገው ህዝብና የፈረስ መስተጋብር እንደማለዳ ጸሀይ ሁልጊዜም ደምቆ የሚነበብ ነው ብለዋል።
ፈረስና የአገው ሕዝብ ቁርኝት ጥንታዊነትን ከዘመናዊነት ጋር አዋድዶ የያዘ መሆኑንም አንስተዋል።
ይህ ታሪካዊና አንጋፋ የሕዝብ ባሕል በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።