ቀጥታ፡

መቅደላ አምባን የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ የሚያስችሉ የመሰረተ-ልማት ሥራዎች ተጀምረዋል

ደሴ፤ጥር 23/2018(ኢዜአ)፡ -መቅደላ አምባን የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ የሚያስችሉ የመሰረተ-ልማት ሥራዎች መጀመራቸው ተገለጸ።

ዩኒቨርስቲው "የመቅደላ አምባ ታሪካዊ ቦታ ቅርስና አካባቢ ጥበቃ ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ የአካባቢው ቱሪዝም ልማት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በደሴ ከተማ አካሂዷል።


 

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ካሳ ሻውል (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፣ ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን የአካባቢውን የቱሪዝም ሀብት በመለየት እንዲለሙ የማድረግ ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው። 

የመቅደላ አምባን ጨምሮ በዩኒቨርስቲው አካባቢ ያሉ የቱሪዝም ሃብቶችንና ታሪካዊ ቦታዎችን በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

አካባቢው በርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሀብቶች እንዳሉት ጠቅሰው፣ ቦታውን ማልማትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲውል የማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውን አመልክተዋል።

በአካባቢው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሙዚየምን ጨምሮ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች እንደሚከናወኑም ነው ያብራሩት።


 

በአማራ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አደመ በበኩላቸው፣ በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊና ባህላዊ የቱሪዝም ሃብቶች በማልማት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሰጡ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም ነባሮቹን ጨምሮ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራው ውጤታማ እየሆነ ነው ብለዋል።

ታሪካዊውን መቅደላ አምባን ጨምሮ ሌሎችንም አካባቢዎች የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የልማት ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።


 

የደቡብ ወሎ ዞን ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አስያ ኢሳ በበኩላቸው፣ በዞኑ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ የዘርፉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የአካባቢውን የቱሪዝም ጸጋ መለየት፣ ማልማትና ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ጠቁመው፣ ታሪካዊውን መቅደላ አምባ በማልማት የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ከትምህርት ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በወሎ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ አሰፋ ባልቻ (ዶ/ር) መቅደላ አምባ አጼ ቴድሮስ አካባቢውን ለመቆጣጠር እንደ ስትራቴጂክ ሥፍራ ይጠቀሙበት እንደነበር አስታውሰዋል።

ሥፍራው የሀገር ክብር፣ ፍቅርና አልሸነፍ ባይነትን የተገለጠበት እንደመሆኑ አካባቢውን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በምክክሩ የዩኒቨርስቲው፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የተለያዩ ዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ አርቲስቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

መቅደላ አምባ አካባቢ ሊጎበኙ የሚችሉ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች መካከል በአጼ ላሊበላ ዘመን ከአንድ አለት ተፈልፍሎ እንደተሠራ የሚነገርለት የፉል አምባ ጊዮርጊስ ውቅር ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው።

በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ይስሃቅ ዘመነ መንግሥት እንደተተከለች የሚታመነው የመቅደላ ማርያም፣ በንጉሥ ሚካኤል የተሠራው እና የንጉሡ አጽም በክብር አርፎ የሚገኝበት ተንታ ሚካኤል ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በውስጣቸውም የኢትዮጵያ ጥንታዊነት የሚዘክሩ እና የሚመሰክሩ በርካታ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች መያዛቸውን ተመልክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም