ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኃይል አማራጭ የልማት ስኬቶች የአፍሪካ ቀንድና የአህጉራዊ የዕድገት መሰረቶች ናቸው - ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የኃይል አማራጭ የልማት ስኬቶች የአፍሪካ ቀንድና የአህጉራዊ የዕድገት መሰረቶች መሆናቸውን የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በተገኙበት የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።


 

በሶማሌ ክልል የተገነባው የአይሻ-2 ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 120 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 80 ሜጋ ዋት ማምረት የሚችለው ምእራፍ በዛሬው እለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በዚሁ ጊዜ የምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያን ልማት በማፋጠን ለአፍሪካ አጠቃላይ ዕድገት እያበረከቱት ላለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አስደናቂ የፕሮጀክቶች ስኬትም የአፍሪካን ልማትና የዕድገት እሴት የሚያንጸባርቁ ቁርጠኛ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማት የማሟላት የልማት ስኬቶች የጎረቤት ሀገራትን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ጭምር ከፍተኛ ፋይዳ እያበረከቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያን የፕሮጀክቶች ስኬት እንደምሳሌ በመውሰድ ቀጣናዊ የልማትና የዕድገት ትብብርን ለማጎልበት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የንፋስ፣ የውሃና ሌሎች የኃይል አማራጭ መሠረተ ልማቶች የአፍሪካ ቀንድና አህጉራዊ አጠቃላይ የዕድገት መሰረቶች ናቸው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለ ሚያደርጉት ጥረት እናመሰግናለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ዕድገትን በማፋጠን ከጎረቤቶቻቸው ጋር በትብብር የሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር አላቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብም ጎረቤት ሀገራት ከጎናቸው ሆነው በትብብር የሚሰሩ ወዳጅ ሀገራት እንዳሏቸው ሊያውቁ አንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም