የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ዲጂታል ክህሎታችንን በማጎልበት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታችንን እያሳደገልን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ዲጂታል ክህሎታችንን በማጎልበት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታችንን እያሳደገልን ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ)፦ የአምስት ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ዲጂታል ክህሎትን በማጎልበት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን እያሳደገላቸው መሆኑን ወጣቶች ገለጹ።
በወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ባለፉት ስድስት ወራት ከ62 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበትን የኢትዮ-ኮደርስ ዲጂታል ክህሎት ስልጠና ማጠናቀቃቸውን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም ያስጀመሩት የአምስት ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እና በኢትዮጵያ መንግስታት የሚተገበር መርሃ ግብር ነው።
በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዌብ ፕሮግራሚንግ፣ ዳታ ሳይንስና በሰው ሰራሽ አስተውሎት መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ላይ 5-ሚሊዮን ወጣቶች በኦንላይን የኮዲንግ ስልጠና እንዲወስዱ ተመቻችቷል።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮም በ5-ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠናን ያጠናቀቁ ወጣቶች የዕውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ካጠናቀቁ ወጣቶች መካከል የአብስራ መርሃፅድቅ፤ ስልጠናው ዘመኑ የሚጠይቀውን የዲጂታል ክህሎት ማበልጸግ የሚያስችል ወሳኝ ዕድል ነው ብላለች።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት አብርሃም ይልቃል በበኩሉ፤ ስልጠናው የዲጂታል ክህሎትን ለማሻሻል የተመቻቸ ዕድል በመሆኑ ሁሉም ወጣት ሊጠቀምበት እንደሚገባ ገልጿል።
ወጣት ታዱ ክፍሌ፤ በበኩሉ የ5 ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን በማሻሻል ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ ሥራ የሚፈጥሩበትን አቅም እንደፈጠረላቸው ገልጿል።
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ዲጂታል ክህሎታችንን በማጎልበት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታችን እያሳደገልን ነው ያለው ደግሞ ወጣት ታሪኩ አዱኛ ነው።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ክብርዓለም ደምሴ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት በወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ከ62 ሺህ በላይ ወጣቶች የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ መነሻነት የስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበትን የቴክኖሎጂ ክህሎት አቅም እንዲገነቡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።