ቀጥታ፡

የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ የኃይል ዋስትና የማረጋገጥ ስትራቴጂያችን አንድ የማዕዘን ድንጋይ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ የኃይል ዋስትና የማረጋገጥ ስትራቴጂያችን አንድ የማዕዘን ድንጋይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በዛሬው እለት ታሪካዊ የሆነውን የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል።

በሶማሌ ክልል የሚገኘው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የኃይል ዋስትና የማረጋገጥ ስትራቴጂያችን አንድ የማዕዘን ድንጋይ ነው ብለዋል።


 

ፕሮጀክቱ ዓመታዊ ኃይል የማመንጨት አቅሙ 467 ጊጋ ዋት በሰዓት (GWh) ሲሆን፤ ዘመናዊ የSCADA እና SVG ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለተረጋጋ የኃይል አቅርቦት እና ለቴክኖሎጂ-መራሽ ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።

የአይሻ ስትራቴጂያዊ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የንፋስ ኮሪደርነቱ ያለፈ ጠቀሜታ እንዳስገኘለትም ተናግረዋል።

ለጎረቤት ሀገራት ያለው ቅርበት ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ንግድ ማዕከል ለማድረግ ለተቀመጠው ግብ መሳካት በተግባር የተረጋገጠ ትልቅ እመርታ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በመደመር መርህ የኢትዮጵያን ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ ወደ የጋራ ሐብት በመለወጥ የአፍሪካ ቀንድን በአካል እና በኢኮኖሚ ይበልጥ ለማስተሳሰር ቁርጠኞች ነን ሲሉም ገልጸዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም