በሶማሌ ክልል ያለውን ሰላም እና ልማት ለማጽናት አበክሮ መስራት ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ያለውን ሰላም እና ልማት ለማጽናት አበክሮ መስራት ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ያለውን ሰላም እና ልማት የበለጠ ለማጠናከር የክልሉ አመራር በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።
የሸበሌ ሪዞርት ዛሬ በይፋ ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የሶማሌ ክልል ከዚህ ቀደም በግጭት እና በጦርነት ይታወቅ የነበረ መሆኑን ተከትሎ አመራሮች ወደ አካባቢው የሚመጡት ለማስታረቅ እና ሰላም ለማስከበር እንደነበር አውስተዋል።
የሶማሌ ክልል በአሁኑ ሰዓት ሰላም ሰፍኖ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ለዚህም የመንገድ ግንባታዎች፣ የማዳባሪያ ፕሮጀክት፣ የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት፣ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ፣ የአየር ማረፊያ ማስፋፊያ ግንባታ እና ዛሬ የተመረቀው የሸበሌ ሪዞርት ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የዛሬውን ቀን በሶማሌ ክልል የሰፈነው ሰላም ትሩፋት ያየንበት ቀን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ እውን እንዲሆን ላደረጉ የክልል አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።
ሰላም ወዳድ የሆነው የሶማሌ ክልል ህዝብ በክልሉ ሰላም እና ልማት እንዲረጋገጥ ወሳኝ ሚና መጫወቱንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት።
አመራሮች ሶማሌ ክልልን ከግጭትና ጦርነት ወደ ሰላም ስላመጣችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እውዳለሁ ብለዋል።
የሸበሌ ሪዞርት በኢትዮጵያ ሁሉም ክልል ልማት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነውም ነው ያሉት።
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነው የሪዞርቱ ግንባታ እንዲሳካ ያደረጉ አመራሮች እና የተለያዩ አካላትን አመስግነዋል።
በሌላ በኩል የጅግጅጋ የኮሪደር ልማት ከተማዋ በምስራቁ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀጣና አንድ ፈርጥ ሆና እየወጣች እንዳለች የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሶማሌ ክልል አመራሮች በሶማሌ ክልል ያለውን ልማት የበለጠ ለማስፋት በላቀ ትጋት እንዲሰሩም አስገንዝበዋል።