የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም መነቃቃት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም መነቃቃት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ)፦ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም መነቃቃት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ የፕሮሞሽን ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተሾመ ተክሉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
ዘርፉ የገንዘብ ዝውውርን በማፋጠን ለኢኮኖሚ መነቃቃት ጉልህ አበርክቶ ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ዓይነተኛ ሚና ያለው መሆኑንም አብራርተዋል።
ከማህበራዊ ትስስር አንጻርም ዜጎች የብሔረሰቦችን ባህል፣ ቋንቋና አኗኗር እንዲረዱ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ መልኩ ዜጎች የሀገራቸውን የታሪክና የተፈጥሮ ቅርሶች በማወቅ በሀገር የመኩራት ስሜትን ከማሳደግ ባሻገር ለአስተሳሳሪ ትርክት ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ የተከበሩት የገና እና የጥምቀት በዓላት ለቱሪዝም ዘርፉ ዕድገት ትልቅ ድርሻ ማበርከታቸው ጠቁመው፤ በበዓላቱ ወቅት የታየው የጎብኚዎች ቁጥር ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ሆኖ መመዝገቡንም ጠቁመዋል፡፡
ቱሪስቶች በዓላቱን ከማክበር ባለፈ በዙሪያው የሚገኙ መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ በማድረግ ለሆቴሎች ገቢ መጨመርና ለዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠር ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ለዘርፉ ዕድገት የራሱን አሻራ እያሳረፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ ልማቱ የከተሞችን ውበትና ጽዳት በመጨመር፣ ነባር መስህቦችን ይበልጥ በመግለጥና አዳዲስ መዳረሻዎችን በመፍጠር የጎብኚዎችን የመሳብ አቅም ማሳደጉን ጠቁመዋል፡፡
የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የተለያዩ የቱሪዝም ዓይነቶችን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
በዚህም የተራራ፣ የውሃ፣ የስፖርት ቱሪዝም እና ሌሎች አዳዲስ ዘርፎች በስፋት እየተለመዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በቀጣይም ከክልሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እነዚህን የቱሪዝም አማራጮች ይበልጥ ለማስፋፋትና ዘርፉን ለማሳደግ በቅንጅት እንደሚሠራ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ በስድስት ወራት ውስጥ ከ32 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በሀገር ውስጥ ቱሪዝም የተሳተፉ ሲሆን ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ እንቅስቃሴ መመዝገቡን አስታውቀዋል፡፡