ቀጥታ፡

ለምርጫው ሂደት መሳካት የዜጎች ተሳትፎ እንዲጎለብት የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እንወጣለን -የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች

ሀዋሳ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምርጫው መሳካት የዜጎች ተሳትፎ እንዲጎለብት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እየሰሩ መሆኑን በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለፁ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ በቁጥር 1113/2011 የመንግሥት አሠራር በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በአሳታፊነት እንዲከናወን ለማድረግ የነቃና በነፃነት የተደራጀ ማኅበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን በማመን ሊወጣ ችሏል።

በአገሪቱ ልማትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው ሚና እንዲጎለብት ለማድረግ እና የተመቻቸ ምህዳር ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን በመረዳትም አዋጁ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ወጥቷል።

በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶችም ዘንድሮ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ሠላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡

የኢየሩሳሌም የሕፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት የሀዋሳና አካባቢው ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ማስረሻ ክብረት ምርጫ ዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን በተሳትፎ የሚያረጋግጡበት የዴሞክራሲ ባህል መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዴሞክራሲ ሊጎለብት የሚችለው ደግሞ የምርጫ ሂደቱ ሠላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ይዘት ሲኖረው እንደሆነ ጠቅሰው ሁላችንም ለዚህ ስኬት የበኩላችንን ጥረት ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡

ድርጅታቸው ከእድሮች፣ ከሴቶችና ወጣት ማህበራት ጋር እንደሚሰራ ገልፀው በነዚህ ተቋማት አማካኝነት ህብረተሰቡ በሀገራዊ ምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የ“ሻይኒ ዴይ” የማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጌታቸው ዘውዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ ሂደት ውስጥ ማህበረሰቡ መብትና ግዴታውን አውቆ በመምረጥም ሆነ በመመረጥ መሳተፍ እንዲችል የግንዛቤ ስራ ይሰራሉ ብለዋል፡፡

ድርጅታቸው ዜጎች በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ ወቅት ሊያከናውኗቸው የሚችሉትንና ማከናወን ያለባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች የማስገንዘብ ፈቃድ ከምርጫ ቦርድ ማግኘቱንም ጠቁመዋል፡፡    

ድርጅታቸው በተለይም ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ማዕከል አድርጎ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚሰራ የገለፁት ደግሞ የ“ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን” ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ግዛቸው ናቸው፡፡

እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች የተሻለ ግንዛቤ ኖሯቸው በተሻለ መንገድ እንዲሳተፉ በማድረግ የምርጫ ሂደቱ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም