ቀጥታ፡

የፋይዳ መታወቂያ አካታች በመሆኑ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው

ሰመራ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ)፦ የፋይዳ መታወቂያ አካታች በመሆኑ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ የንቅናቄ መርሃ ግብር በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።


 

በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን ፋይዳ መታወቂያ አካታች በመሆኑ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

በተያዘው ዓመት 30 ሚሊየን ሴቶችና 10 ሚሊየን ህፃናት የመታወቂያው ባለቤት ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አንስተው ዕቅዱን ለማሳካት በቁርጠኝነት ይሰራል ነው ያሉት።

የፋይዳ መታወቂያ አካታችነት ሴቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበት፣ መብቶቻቸውን ማረጋገጥ የሚችሉበትና የሴቶችና ህፃናትን ክብርና ጥቅም ማሳደግ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው የፋይዳ መታወቂያ የሴቶችን መብት ከማስጠበቅ አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።

ሴቶች እንደ ሀገር ያላቸው ሁለንተናዊ ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው የፋይዳ መታወቂያም ይህንኑ ተሳትፏቸውን በማጎልበት ተጠቃሚነታቸውን ዕውን ለማድረግ አይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ምክትል ዋና ዳይሬክተር ራሄል አብርሃም እንደገለጹት የፋይዳ መታወቂያ ስርዓት መዘርጋት ዜጎች በፍትሃዊነት እንዲገለገሉ መደላድል ፈጥሯል።

ዘንድሮ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ከ100 በላይ በሚሆኑ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት 90 ሚሊየን የሚሆኑ ተጠቃሚዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም