የሸበሌ ሪዞርት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የገባነውን ቃል በተግባር ያረጋገጠ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሸበሌ ሪዞርት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የገባነውን ቃል በተግባር ያረጋገጠ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ የሸበሌ ሪዞርት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የገባነውን ቃል በተግባር ያረጋገጠ የምስራቁ የሀገራችን ክፍል ትልቅ ሥራ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ከ’ገበታ ለትውልድ’ ዐቢይ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለተኛውንና በ385 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውን የሸበሌ ሪዞርት ተመርቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል።
ሪዞርቱ መዝናኛ ስፍራ ብቻ ሳይሆን፤ የዘመናዊ ሥነ-ሕንጻ ጥበብን ከሶማሌ ክልል ባሕላዊ እሴት ጋር አቀናጅቶ የያዘ የታሪክ ማኅደር ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የገባነውን ቃል በተግባር ያረጋገጠ የምስራቁ የሀገራችን ክፍል ትልቅ ሥራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በክልሉ የሚገኘው እጅግ ሰፊ እና ማራኪ ተፈጥሯዊ ጸጋ በመደመር ዕሴትና ትብብር ወደ ልማት ሲለወጥ፤ ኢትዮጵያ የምታልም ብቻ ሳትሆን ህልሟን ወደ እውነት የምትቀይር እና የምትኖር ሀገር መሆኗን በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል።