በዞኑ አርብቶ አደሩን በማሳተፍ ከ33 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ አርብቶ አደሩን በማሳተፍ ከ33 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ነው
ጂንካ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ):- በደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደሩን በማሳተፍ ከ33 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃና የግጦሽ ሳር መከለል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ ምንላርገው አዲሱ፣ በዞኑ በተጀመረው የተፋሰስ ንቅናቄ ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት 50 ንዑስ ተፋሰሶች የማልማት ስራ እንዲሁም በአርብቶ አደርና በዝቅተኛ አካባቢዎች ደግሞ ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የግጦሽ ሳር መከለል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ በዞኑ ከ33 ሺህ ሄክታር መሬት የተፋሰስና የግጦሽ ሳር መከለል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ የተፋሰስ ልማቱ በተከናወነባቸው ስፍራዎች ከ11 ሚሊየን በላይ ሀገር በቀል ችግኞች ተከላ ይከናወናል ነው ያሉት።
በዘንድሮው ዓመት የተፋሰስ ልማት በሳይንሳዊ ጥናት የተደገፈ ስነ-አካላዊና ስነ-ህይወታዊ ስራዎች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል።
ልማቱ የተከናወነባቸው አካባቢዎችን ከሰውና ከእንሰሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በዞኑ ሐመር ወረዳ እየተከናወነ ባለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተሳተፉት ወይዘሮ አልጎ በሌ፥ በአካባቢው የቡስካ ጥብቅ ደን እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ደኑ በሰውና በእንስሳት ጉዳት ይደርስበት እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ደኑን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ የመጠበቅ ስራ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በአካባቢያችን የተፋሰስ ልማት ከተጀመረ ወዲህ አካባቢው ለእርሻ ተስማሚ መሆን ጀምሯል ያሉት አቶ አስ ኦቶሎ ለእንስሳት የሚሆን በቂ የግጦሽ ሳር የምናገኝበት ዕድልንም እየፈጠረ ነው ብለዋል።