የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ልማት ሽግግር ከማፋጠን ባሻገር የቀጣናውን ሀገራት የኃይል ትስስር በማሳደግ የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ልማት ሽግግር ከማፋጠን ባሻገር የቀጣናውን ሀገራት የኃይል ትስስር በማሳደግ የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያስገኘ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ በራስ አቅም የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ልማት ሽግግር ከማፋጠን ባሻገር የቀጣናውን ሀገራት የኃይል ትስስር በማሳደግ የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያስገኘ እንደሚገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት÷ የውሃ ሃብት የኃይል አቅርቦትና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማሳለጥ ወሳኝ ነው።
የኢትዮጵያ የከተማና ገጠር የኢንዱስትሪና የግብርና ልማት ስኬትም በውሃ ሃብቶች የተገነቡ የኃይልና የመስኖ መሠረተ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማና ገጠር የኃይል ሥርጭት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም ዘላቂ የውሃ ሃብት አስተዳደር ልማት በትኩረት የሚሰራባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት በእጥፍ አሳድጓል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህም አሁን ላይ ኢትዮጵያ 9 ነጥብ 6 ጊጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንድትፈጥር አስችሏታል ብለዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት 1 ነጥብ 1 ጊጋ ዋት ኃይል በማመንጨት በከተማና ገጠር የኢንዱስትሪና ግብርና ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገብ እንደተቻለ ገልጸዋል።
ከዋናው የኃይል ማስተላለፊያ አካባቢ በርቀት የሚኖሩ ዜጎችም በጸሐይ፣ በነፋስና በባዮ ጋዝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
በዜጎች ተሳትፎ በራስ አቅም የተገነባው የሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካውያን ትልቅ ትምህርት የሰጠ የኩራት ምንጭ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያንም ጫናዎችን በመቋቋም ሕዳሴን ማጠናቀቃቸው ለአፍሪካውያን በራስ አቅም የመልማት ፋና ወጊነትን በተግባር ማሳየት ማስቻሉን ተናግረዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብም የኢትዮጵያ ልማት ሽግግር ከማፋጠን ባሻገር የቀጣናውን ሀገራት የኃይል ትስስር በማሳደግ የጋራ የኢኮኖሚ በረከት እያስገኘ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዚህም በጥቂት ዓመታት 21 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማት በመገንባት ጎረቤት ሀገራትን ማስተሳሰር ያስቻለ ስኬት እንደተገኘ ገልጸዋል።
ይህም የኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይል ትስስር የጎረቤት ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት አቅማቸውን በማሻሻል ዕድገታቸውን የሚያፋጥኑበት ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሕዳሴ ግድብ ለታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት አስተማማኝ የውሃ ፍሰት በማስገኘት ከጎርፍ አደጋ እየታደጋቸው እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በዓሳ፣ ቱሪዝምና ሌሎች መስኮች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል በንጋት ሃይቅና ዳርቻው የተቀናጀ ማስተር ፕላን እንደሚተገበር አንስተዋል።
በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍም በአጠቃላይ 80 ነጥብ 4 ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍሎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ያስቻለ አመርቂ ስኬት ማምጣት እንደተቻለ ገልጸዋል።