ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በ86ኛው ዓመት የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል አከባበርና አስደናቂውን የፈረስ ትዕይንትን ይታደማሉ

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በ86ኛው ዓመት የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል አከባበርና አስደናቂውን የፈረስ ትዕይንትን እንደሚታደሙ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የጀግኖች ምድር፣ የደግነት፣ የአብሮነትና የፍቅር መገለጫ፤ በልምላሜዋና በሁሉን አምራችነቷ የምትታወቀው የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና ከተማ እንጅባራ ገብተናል ብለዋል።


 

"አዲናስ" ብሎ በፈገግታ የተቀበለንን፣ እንግዳን እንደ ፈጣሪ ስጦታ አክብሮ የማስተናገድ ጥንታዊ ባህሉንና ፍቅሩን በተግባር ላሳየን የአገው ምድር ሕዝብ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ላሳያችሁን ፍቅርና ክብር ያለን አክብሮት ላቅ ያለ ነው ሲሉም ገልጸዋል።


 

በቆይታቸውም የኢትዮጵያ አንዱ ጌጥና ኩራት የሆነውን፣ የአዊን የጀግንነት ታሪክ፣ ባህልና ወኔ የሚመሰክረውን የ86ኛው ዓመት የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል አከባበርና አስደናቂውን የፈረስ ትዕይንት እንደሚታደሙ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም