ቀጥታ፡

የጣሊያን ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018(ኢዜአ)፦ የጣሊያን ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ ገለጹ።

አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ እና ጣሊያን የቆየና ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አስታውሰው፤ የጣሊያን መንግስት ለኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የጣሊያን መንግስት የኢትዮጵያን የልማት ጥረት በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማገዝ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይም የማቴይ እቅድ (Mattei Plan) በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ስልታዊ ትብብር ለማጠናከር አርቆ አሳቢ መድረክ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የሪፎርም እና የልማት ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ የገለጹት አምባሳደሩ፣ የጣሊያን ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ጣሊያን በአውሮፓ ህብረት እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያን ለመደገፍ የምታደርገውን ጥረት ታጠናክራለች ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለውና ተነሳሽነቱ ከፍ ያለ ወጣት የሰው ኃይል ባለቤት መሆኗን ጠቁመው ይህን አቅም ለመጠቀም ትምህርት፣ የክህሎት ልማት፣ ሳይንሳዊ ምርምር፣ የባህል ልውውጥና የታሪክ ጥበቃ የትብብሩ ዋና ማዕከል መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ጣሊያን የኢትዮጵያ ታሪካዊና አስተማማኝ አጋር ሆና እንደምትቀጥል አረጋግጠው፤ የሀገሪቱን የልማት ተስፋ በዘላቂነት ለመደገፍ የላቀ ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ ገልጸዋል።

ወቅታዊው የዓለም ሁኔታ ውስብስብ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የዲፕሎማሲያዊ ውይይትና የሁለትዮሽ ግንኙነት ሚና ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ በመጪው የካቲት 6 ቀን 2018 ዓ.ም (February 13, 2026) በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የጉባኤው ዋና የትኩረት ዓላማዎችም ዘላቂ ልማት፣ መሰረተ ልማት፣ ኢነርጂ፣ ትምህርትና ስልጠና፣ ጤና እና ግብርና ሲሆኑ የጣሊያንና የአፍሪካ ስልታዊ አጋርነት ማዕቀፍ የሆነውን "የማቴይ እቅድ" (Mattei Plan) ይበልጥ ማሳደግ መሆኑ ታውቋል።

በጉባኤው እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶች የሚገመገሙ ሲሆን፣ ለቀጣይ የጋራ ስራዎችም አዳዲስ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም