ቀጥታ፡

የእርሻ መሬትን በአግባቡ በማልማት ከአርሶ አደሩ ተጣቃሚነት ባለፈ ለኢንዱስትሪ እና ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን ምርት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

አዳማ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የእርሻ መሬት በአግባቡ በማልማት ከአርሶ አደሩ ተጣቃሚነት ባለፈ ለኢንዱስትሪ እና ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን ምርት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሜካናይዜሽን እና የከተማ ግብርና ስትራቴጂ ማብሰሪያ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ እንዳስታወቁት በሀገሪቱ በግብርና ሊለማ የሚችል ከ38 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ይገኛል።

እስካሁን የለማው መሬት ከግማሽ ያልዘለለ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል ከአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ባለፈ ለኢንዱስትሪ እና ለዓለም ገበያ ለሚቀርበውን ምርት ለማሳደግ ግብ ተይዞ እተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓት ለማቅረብ እና ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ግብርናውን በማዘመን የመስኖ አጠቃቀምን በማስፋፋት ኤክስፖርት መር ለማድረግ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የግብርና ሜካናይዜሽን እና የከተማ ግብርና ዋነኞቹ የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተለይ የከተማ ግብርና በከፍተኛ ንቅናቄ በመመራቱ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ፣ ሰፊ የስራ እድል የመፍጠር እንዲሁም የተሻለ ሥርዓተ ምግብ ከመፍጠር አኳያ ጥሩ ጅምር ስራዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ይህንን ጅምር ለማጠናከር ስትራቴጂዎች መነደፋቸውን ገልጸዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽንን እወን ለማድረግም ለሜካናይዜሽን ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው፤ ሜኬካናይዜሽን ከመሬት ዝግጅት እስከ ምርት መሰብሰብ ብሎም የድህረ ምርት ብክነተን በማስቀረት ምርትማነተን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የግብርና ሜካናይዜሽንን የሚያሳልጡ መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ እና በአነስተኛ ወለድ ለአርሶ አደሮች እንዲተላለፉ በማድረግ ምርታማነታቸውን ለማሻሻል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ማቲዎስ ሰቦቃ በበኩላቸው የከተማ ግበርናን ለማስፋፋት በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

ከ10 ሺህ በላይ ሼዶችን በመገንባትና በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች በማስተላለፍ የከተማ ግብርንና የሌማት ትሩፋትን ማስፋፋት መቻሉን ተናግረዋል።

የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮቹ በአዳማ የከተማ ግብርና ልማት ስራዎችን ጎብኝተው የግብርና ኤግዚብሽንም ተከፍቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም