ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አስተዳደርን በማጠናከር በኩል እያከናወነችው ያለው ተግባር አበረታች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አስተዳደርን በማጠናከር በኩል እያከናወነችው ያለው ተግባር አበረታች መሆኑን የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት(ILO) የኢትዮጵያና የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ኩምቡላ ንዳባ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የተደራጀ እና ሕጋዊ የሥራ ስምሪትን ለማጠናከር ያለመ አዲስ ፕሮጀክት ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ከአውሮፓ ህብረት ባገኘው ድጋፍ ይፋ አድርጓል።


 

"በኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ሕጋዊና ሥርዓት ያለው የሠራተኞች ፍልሰት እንዲኖር ክልላዊ ትብብርን ማጠናከር" በሚል መሪ ሀሳብ የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት፤ በዛሬው ዕለት ምክክር ተደርጎበታል።

የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት(ILO) የኢትዮጵያና የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ኩምቡላ ንዳባ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የሠራተኞችን መብት ለማስከበርና ሕጋዊ የጉዞ መንገዶችን ለማመቻቸት ያሳየችውን መሻሻል አድንቀዋል።

ለአራት ዓመታት የሚቆየው ይህ ፕሮጀክት ወቅታዊ፣ ተዓማኒና የተከፋፈለ የስደት መረጃን በማደራጀት የመንግስትን የውሳኔ አሰጣጥ አቅም ማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትን በማጠናከር ለዜጎች በውጭ ሀገር እውቅና የሚኖረው የክህሎት ማረጋገጫ መስጠትና ተወዳዳሪነታቸውን መጨመር እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የቅጥር ኤጀንሲዎችን አሠራር በመቆጣጠርና የሕግ ማዕቀፎችን ተግባራዊ በማድረግ በሠራተኞች ላይ ሊደርስ የሚችለውን በደል መከላከል የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል ከፍልሰት ተመላሾች ትክክለኛ መረጃና የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡


 

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብርሃኑ አለቃ እንደገለጹት፤ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።

ይህ ፕሮጀክትም ዜጎች በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለሚደርስባቸው እንግልት እንደ ትልቅ መፍትሔ እንደሚታይ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢሠማኮ) ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ ፕሮጀክቱ ሠራተኞች ወደ ውጭ ከመሄዳቸው በፊት፣ በቆይታቸው እና ሲመለሱ የተሻለ ድጋፍ ማግኘት የሚያስችላቸውን ተቋማዊ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ኢሠማኮ ለስኬታማነቱ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የአውሮፓ ህብረት የፕሮግራም ኦፊሰር ሉቦሚራ ሚሬሶቫ፤ ህብረቱ ኢትዮጵያ የሠራተኛ ፍልሰት አስተዳደርን ለማጠናከር ላደረገችው ጥረት እውቅና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።


 

ፕሮጀክቱ ሕጋዊ የፍልሰት መንገዶችን ተደራሽ በማድረግ ወጣቶች መደበኛ ላልሆኑ ጉዞ፣ ለሞትና ለብዝበዛ እንዳይጋለጡ ጥበቃ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም