ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚከናወነው 2ኛው ዙር የኮሪደር ልማት የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ማጎልበት የሚያስችል ባዛር ይካሄዳል

አሶሳ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚከናወነው 2ኛ ዙር የኮሪደር ልማት የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ማጎልበት የሚያስችል ባዛር እንደሚካሄድ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ባዛሩ በክልሉ በአሶሳ፣ ግልገል በለስ፣ ባምባሲና ካማሺ ከተሞች ለሚከናወነው 2ኛ ዙር ኮሪደር ልማት ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ገርቢ ሎላሳ  በሰጡት መግለጫ፣ በክልሉ በአሶሳ በመጀመሪያ ዙር በተከናወነው የኮሪደር ልማት ሕብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ይህም ከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው መነቃቃቱንና በሕብረተሰቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት መፍጠሩን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ 2ኛው ዙር የኮሪደር ልማት በአሶሳ ከተማ በፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በግልገል በለስ፣ ባምባሲና ከማሺ ከተሞች ለተጀመረው የኮሪደር ልማት የገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ባዛሩ ከጥር 25 ቀን 2018 ዓ-ም ጀምሮ ለአንድ ወር ያክል በሚቆየው ባዛር ስፖርታዊ ውድድሮች፣ የተለያዩ ጨረታዎች ፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ ቶምቦላ ሎተሪን ጨምሮ የተለያዩ መርሃ-ግብሮች እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል፡፡ 

ከንግዱ ማኅበረሰብ ተሳትፎ እና ከገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን የገለፁት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም