ቀጥታ፡

በቤንች ሸኮ ዞን በበልግ እርሻ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል

ሚዛን አማን፣ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡-በቤንች ሸኮ ዞን በበልግ እርሻ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን የዞኑ ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ገለጸ።

በዞኑ በ2018/19 የበልግ እርሻ ከ118 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት ለማልማት የታቀደ ሲሆን እቅዱን ለማሳካት በሚዛን አማን ከተማ የንቅናቄ መድረክ  ተካሄዷል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሳሙኤል አሰፋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዞኑ በበልግ እርሻ የሚታረሰው መሬት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሆን ዘንድሮ ለማልማት የታቀደው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ10 ሺህ ሔክታር ብልጫ አለው።


 

በዞኑ ጾም የሚያድር መሬትን ዜሮ የማድረግ ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ የተጀመረው ስራ እንደሚጠናከር ተናግረዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን ማስፋፋትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ ትኩረት ከተሰጡት ተግባራት መካከል ነው ብለዋል።

በዞኑ ሩዝ፣ በቆሎ፣ ማሽላና ሌሎች ዋና ዋና ሰብሎችን ጨምሮ የሆርቲካልቸር ምርቶች በስፋት የሚመረት ሲሆን ዘንድሮ ከሚለማው 118 ሺህ 409 ሔክታር መሬት ላይ ከ9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደግፌ ኩድን በበኩላቸው በዞኑ ሊታረሱ የሚችሉ መሬቶችን ለይቶ በማልማት በምግብ ራስን ከመቻል የተሻገረ ምርት መሰብሰብ  ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የሼይ ቤንች ወረዳ ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ቃዴስ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአርሶ አደሩ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ይህም ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ በመሆኑ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን የማቅረብ ስራ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።


 

ጾም የሚያድሩ መሬቶችን በአርሶ አደሩና በተቋማት ደረጃ እንዲለዩ እየተደረገ ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ቤንች ወረዳ ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት መምሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል መኩሪያ ናቸው።

የመንግስት የልማት ስትራቴጂን ለማሳካት በየደረጃው ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን አስፈላጊ በመሆኑ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።


 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም