ቀጥታ፡

ዩኒቨርስቲው ችግር ፈቺ ምርምሮችን ወደ ተግባር ለመቀየር ከባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራል

ደሴ ኢዜአ ጥር 22/2018-የወሎ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ወደ ተግባር ለመቀየር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው "ተግባራዊ ምርምር ለዘላቂ ሀገራዊ ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ 12ኛውን ዓመታዊ የምርምር ኮንፈረንስ በደሴ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን የሕብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርስቲው በጤና በትምህርት፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቴክኖሎጂ፣ በባህልና ኪነጥበብ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በሌሎችም ዘርፎች ያካሄዳቸው የምርምር ውጤቶች ወደ ተግባር ተቀይረው ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ለውጤታማነቱም ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ከዞንና ከከተማ አስተዳደር ተቋማትና አስፈጻሚ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።


 

በዩኒቨርስቲው ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጢጣ ልዕለ ህክምና ካምፓስ ሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ ጌታው ዋለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ለተግባራዊ ምርምር በተሰጠ ትኩረት የህብረተሰቡን ችግር ማቃለል መቻሉን አንስተዋል።

የሴቶችን፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲሁም የእናቶች ጤና ክብካቤ ማሳደግ ላይ ያተኮረ ጥናት ማካሄዳቸውንም አመልክተዋል።

ይህም ጥናት ወደ ተግባር ለመቀየር ከጊዜ ሰሌዳ ጀምሮ እቅድና መመሪያ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም