ቀጥታ፡

በክልሉ በተቀናጀ የህብረተሰብ ተሳትፎ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በተሰራው ስራ ውጤት ተገኝቷል

ዲላ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  በተቀናጀ የህብረተሰብ ተሳትፎ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በተሰራው ስራ ውጤት መገኘቱን የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎‎በክልሉ የትራፊክ አደጋን መከላከልን ያለመ የምክክር መድረክ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ብርሃኑ ጌቦ (ዶ/ር) በወቅቱ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ የትራፊክ አደጋ የሚያደርሰውን ሰብዓዊ፣ ቁሳዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ለመቀነስ በተደረገ የተቀናጀ ጥረት ውጤት ተገኝቷል።

ለአብነትም ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ በተከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች የደረሱ የሞትና የአካል ጉዳት አሃዝ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ28 በመቶ መቀነሱን ተናግረዋል።

ለዚህም የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትን ብቃት ማሻሻልና ከደረጃ በታች የሆኑትን መዝጋት፣ ለነባር አሽከርካሪዎች ስልጠና መስጠትን ጨምሮ የግንዛቤ ስራዎች መጠናከር ለተገኘው ውጤት ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ለማደራጀት በተደረገ ጥረት በ16 መናኸሪያዎች የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት መሰጠት መጀመሩንም አንስተዋል።

በዲላ፣ በወላይታ ሶዶና በአርባምንጭ ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ የዘመናዊ መናኸሪያዎች ግንባታ መጀመሩን አንስተው ይህም የተቀላጠፈ የትራንስፖርት አገልግሎትን ከማቅረብ በተጓዳኝ አደጋን ለመቀነስ ድርሻው የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት።

የትራፊክ አደጋው እየቀነሰ ቢመጣም ችግሩ አሁንም አሳሳቢ በመሆኑ ቅንጅታዊ ስራው ይበልጥ መጠናከር እንደሚገባውም ጠቁመዋል።

ለትራፊክ አደጋው መስፋት የአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ፣ የሥነ ምግባር ችግር፣ ትርፍ መጫን እንዲሁም በፍጥነት ማሽከርከር ተጠቃሽ መንስኤዎች መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ መከላከልና ፍሰት ቁጥጥር ዳይሬክተር ኮማንደር ለማ ለቾሬ ናቸው።


 

ችግሩን ለመቀነስም የፍሰት ተቆጣጣሪዎችን አቅም ከማጎልበት ባለፈ የትራፊክ ደህንነት ክበባትን በማስፋት አደጋን ለመቀነስ በተደረገው ጥረት ውጤት መገኝቱን አንስተዋል።

የትራፊክ አደጋን በዘላቂነት ለመቀነስ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የጫሞ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርት ሰናይት አስታጥቄ በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ በተከታታይነት በሚሰጥ የመንገድ ደህንነት ትምህርት ተማሪዎች በዘርፉ የተሻለ ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን ገልጸዋል።


 

በተለይ ትምህርት ቤቱ ዋና መንገድ ላይ የሚገኝ ቢሆንም በተማሪዎች ዘንድ ትክክለኛ የመንገድ አጠቃቀም ልማድ መዳበሩ የትራፊክ አደጋ ተጋላጭነት መቀነሱን ተናግረዋል።

እንዲሁም ከ20 የሚልቁ ተማሪዎች የተማሪ ትራፊክ ፖሊስ ስልጠና በመውሰድ በመውጫና መግቢያ ሰዓት የትራፊክ እንቅስቃሴውን የማሳለጥ ሥራን በማገዝ የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም