በክልሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተሰጡ አቅጣጫዎች መሰረት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ፍጥነትና ፈጠራን መሰረት ባደረገ መልኩ ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተሰጡ አቅጣጫዎች መሰረት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ፍጥነትና ፈጠራን መሰረት ባደረገ መልኩ ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018(ኢዜአ)፦ በሀረሪ ክልል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተሰጡ አቅጣጫዎች መሰረት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ፍጥነትና ፈጠራን መሰረት ባደረገ መልኩ እናስቀጥላለን ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።
በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በመደመር መንግሥት እይታ የዘርፎች እመርታ ሥልጠና ማጠቃለያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተሰጡ አቅጣጫዎች ግቦች አፈፃፀም ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱም አቶ ጌቱ ወዬሳ እንዳሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተሰጡ አቅጣጫዎች መሰረት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት በውጤታማነት እንዲቀጥሉ አመራሩ በቁርጠኝነት ይሰራል።
በክልሉ በተለይም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፤ የቅዳሜ እና የእሁድ ገበያን በማስፋፋት አምራችና ሸማችን በማገናኘት እንዲሁም የቁጥጥርና ክትትል ስራዎች በማጠናከር የኑሮ ውድነት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
የዲጂታላይዜሽን አሰራሮችን በማሳደግ እንዲሁም ተጠያቂነትን በማስፈን፤ የሰላም እሴት ግንባታ ስራዎች የማሳደግ እንዲሁም ጠባቂነትን ለመቀነስ እየተደረጉ የሚገኙ ርብርቦችን አጠናክረን እናስቀጥላለን ነው ያሉት።
ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ በክልሉ የሚታረስ መሬት ፆሙን እንዳያድር የማድረግ፤ በምግብ ራስን ለመቻልና ከተረጂነት ለመላቀቅ እንዲሁም ኮንትሮባንድንና የመሬት ወረራንና ህገወጥ ግንባታን ዜሮ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎች የበለጠ ይጠናከራሉ ብለዋል።
የገጠር ኮሪደር፣ የምርት ማከማቻ ግንባታን የማፋጠን፣ የሽያጭ ማዕከልና አግሮ ፕሮሰሲንግ ግንባታ እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስፋት እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ፍጥነትና ፈጠራ በታከለበት መልኩ እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
የሌማት ትሩፋትን በማስፋት፣ የበጋ እርሻና የኩታ ገጠም ስራዎችን የማሳደግ እንዲሁም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የማሳደግ፤ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ተገቢው ድጋፍ በማድረግ እንዲጎለብት ማስቻል፤ የማዕድን ዘርፉ ላይ ያሉ ሀብቶችን ለመጠቀም የሚሰሩ ስራዎች እንዲሁ ይጠናከራሉ ነው ያሉት።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በማጠናከር ኢንዱስትሪዎችን የማሳደግ ስራ ላይም እየተሰሩ የሚገኙ ጅምር ስራዎችን ለማሳደግም ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተግባራዊ ስለመሆናቸው የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራም ነው አቶ ጌቱ ያስገነዘቡት።