ቀጥታ፡

ቦርዱ እያከናወናቸው ያሉ የሕግና የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎች ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሂደት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እያከናወናቸው ያሉ የሕግና የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎች ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሂደት ይበልጥ ዴሞክራሲያዊነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ፡፡

7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሐሳብ የበላይነት እና በሕዝብ ይሁንታ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲካሄድ የጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱ ይታወሳል።

በዚህም የዕጩዎች ምዝገባ ከጥር 1 እስከ የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲሁም የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ይከናወናል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ምርጫው ሰላማዊና ስኬታማ እንዲሆን ምክር ቤቱ ልዩ ዕቅድ አውጥቶ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሰፊ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰው፣ ለዚህም በቢሾፍቱ የተደረሰው የሰላም ቃል ኪዳን እንደ ትልቅ ስኬት እንደሚጠቀስ አስረድተዋል።

ምርጫው ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን አድንቀው፣ በተለይም በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ማሻሻያ አዋጅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዋጁ መሻሻል ችግሮችን በንግግር መፍታት እንደሚቻል ያሳየና ለነፃ ምርጫ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነውም ብለዋል።

በተጨማሪም የዘንድሮውን የዕጩዎች ምዝገባ ለየት የሚያደርገው በዲጂታል ዘዴ መከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ጉዞ የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።

7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሀገሪቱ በብሔራዊ ምክክር እና በፖለቲካዊ መረጋጋት ሂደት ውስጥ ባለችበት ወቅት መከናወኑ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

ሰላምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ሁሉም ፓርቲዎች ሕግና ሥርዓትን አክብረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ለትውልድ የሚተላለፍ ጠንካራ ሀገር እና ነፃ የዴሞክራሲ ባህል መገንባት የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ኃላፊነት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ምክር ቤቱ ምርጫው ፍፁም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ከመንግስት ጋር በቅንጅት መስራቱን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም