የአርበኞችን ታሪክና የፈረስን ውለታ የሚዘክረው የአገው ፈረሰኞች በዓል ነገ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የአርበኞችን ታሪክና የፈረስን ውለታ የሚዘክረው የአገው ፈረሰኞች በዓል ነገ ይከበራል
ባሀርዳር ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያውያን አርበኞችን ታሪክና የፈረስን ውለታ የሚዘክረው የአገው ፈረሰኞች 86ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ነገ በተለያዩ ክዋኔዎች በእንጅባራ ከተማ እንደሚከበር የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
በዓሉን በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም ተመልክቷል።
የአማራ ክልል ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) በዓሉን አስመልክቶ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ጊዜ የአገው ፈረሰኞች በዓልን በመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ የሰው ልጆች ወካይ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ብለዋል።
86ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ሆነን የምናከብረው ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን አርበኞችን ታሪክና የፈረስን ውለታ የሚዘክረው በዓሉ "የአገው ፈረስ ባህል" በሚል ስያሜ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ሰነዶች መቅረባቸውንም ገልጸዋል።
በሰነዱ ከተካተቱ ጉዳዮች ውስጥ ፈረስ ከአገው ህዝብ ጋር ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቁርኝት በዋነኝነት እንደሚጠቀስ አስረድተዋል።
በዓሉ የፈረስ ግልቢያና የፈረስ ላይ ትርዒቶችን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች የሚካሄዱበት መሆኑንም አንስተዋል።
የአገው ፈረሰኞች በዓል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ስር በሚገኙ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር ባለፈረሰኞች በማህበራቸው አማካኝነት በአንድ ቦታ በመሰባሰብ በየዓመቱ የሚያከብሩት ታላቅ በዓል ነው።
በዓሉን ለመታደምም ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎችና የውጭ ሀገራት የመጡ ጎብኚዎች ወደ እንጅባራ ከተማ እየገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።
86ኛው የአገው ፈረሰኞች ማህበር "የአብሮነት ቅርስ፣ የሰላም ውርስ" በሚል መሪ ሀሳብ ነገ በእንጅባራ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።