ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ድጋፍና ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ድጋፍና ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ
ቦንጋ፣ጥር 22 /2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍና ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ።
የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ማህበራትንና የህዝቡን የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል።
ይህን እውን ለማድረግም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባደረገው የተቀናጀ ጥረት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሳተፉ በማድረግ አጀንዳቸውን እንዲሰጡ ሲያደርግ ቆይቷል።
በዚህም አጀንዳ የመሰብሰብና በሀገር አቀፉ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣን አጠናቆ ለቀጣይ ምዕራፍ በዝግጅት ላይ ይገኛል።
በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች እንዳሉት ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ እና ተሳትፎአቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን መኮንን ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ በተጀመረው ተግባር በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢዜማ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳውን ከመስጠት ባለፈ ለስኬቱ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል።
በየደረጃው በተካሄዱ የውይይት መድረኮች ላይ ያለምንም ተፅእኖ ሀሳባቸውን እንዲገልፁ መደረጉ የኮሚሽኑን ገለልተኝነትና አካታችነት ያረጋግጣል ብለዋል።
በሀገር ጉዳይ ላይ በመወያየት የልዩነት ሃሳቦችን በመፍታት በጋራ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለሀገር ልማት የሚውሉበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ምክክሩ ዓይነተኛ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል።
በምክክር ሂደቱም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በፍትሐዊነት እንዲሳተፉ እየተደረገ ያለው ጥረት ለሀገራችን አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ገልፀዋል።
የካፋ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት (ካህዴህ) ሰብሳቢ አቶ ቦጋለ ሀይሌ በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ሰላሟ የተረጋገጠ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፓርቲያቸውም ለምክክሩ ስኬታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
ምክክሩ በሀገር ጉዳይ በጋራ በመወያየት ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የምንሸጋግረበት ትልቅ ዕድል ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) የክልሉ ሰብሳቢ መቅደስ መኮንን ናቸው።
ምክክር ኮሚሽኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሲቪክ ማህበራት እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን የፍትሐዊነቱና እና አሳታፊነቱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ፓርቲው አጀንዳውን ከመስጠት ባለፈ የኮሚሽኑን ተግባር በቅርበት በመከታተል ገንቢ ሀሳቦችን እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል።
በሀገራዊ ጉዳይ ላይ በመተባበር መስራት የግድ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ ለዚህም ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።