ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን ህዳሴ ግድብ ግንባታን በራሳቸው አቅም ማጠናቀቃቸው ለአፍሪካውያን ትልቅ ድል ነው

አዲስ አበባ፤ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፦ዓለም ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የፋይናንስ ድጋፍ ቢከለክልም ግድቡን በራሳቸው አቅም ማጠናቀቃቸው ለአፍሪካውያን ትልቅ ድል ነው ሲሉ የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌይ ገለጹ።

የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌይ ታዋቂው ደቡብ አፍሪካዊ ኮሜዲያን፣ ፀሐፊ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ትሬቨር ኖሃ በሚያዘጋጀው "What Now?" ፖድካስት ላይ ቆይታ አድርገዋል።

ትሬቨር ኖህ በውይይቱ ወቅት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ቀጣናዊ የኢነርጂ ትስስር እና በኢትዮጵያውያን አቅም መገንባቱን አጽንኦት ሰጥቶ ተናግሯል።


 

የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፥ ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንዳላት እና ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ የሀገሪቷ ዜጎች ብቻ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ህዳሴ ግድብ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አድዋ እንደሆነ በግድቡ ምርቃት ወቅት እንደነገሯቸው አውስተው፥አድዋ ኢትዮጵያ ማንም ሊያምን የማይችለውን ተአምራዊ ድል በጣልያን ላይ ያስመዘገበችበት እንደሆነ ተናግረዋል።

አድዋ ለፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ መጀመር በር የከፈተ እና የጥቁር ህዝቦች ለዘመናት ከነበሩበት ጭቆና ተላቀን ነጻነታችንን ማረጋገጥ አለብን ብለው ለጀመሩት ትግል ትልቅ ስንቅ ሆኗቸዋል ነው ያሉት።

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለግድቡ የፋይናንስ ድጋፍ መከልከሉን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፥ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም ግድቡን እንገነባለን ብለው መነሳታቸውን ተናግረዋል።

ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት ከሁሉም በላይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ገንዘብ በማዋጣት ግድቡ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።

ዓለም ለድጋፍ እምቢ ቢልም ኢትዮጵያውያን 14 ዓመታት ቢፈጅባቸውም ግድቡን በራሳቸው አቅም ገንብተው ጨርሰውታል ነው ያሉት።

ይህ ለዘመናት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በራሳቸው አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት አይችሉም የሚለውን የኃያላን ሀገራት የዘመናት የቆየ ትርክት እንዲቀየር ማድረጉን ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የአይበገሬነት እና የጽናት ታሪክ ነው ብለዋል።


 

ይህ ለአፍሪካውያን ትልቅ ድል መሆኑን ገልጸው፥ አፍሪካውያን ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በራሳቸው መገንባት ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የህዳሴ ግድብ የምህንድስና ልህቀት የታየበት ግድብ እና የአፍሪካ ትልቁ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ መሆኑን ገልጸዋል።

የግድቡ ርዝመት እና ከፍታ እንዲሁም ውሃ የሚፈስበት ፍጥነት እና ኃይል እጅጉን አስገራሚ እንደሆነ ጠቅሰው ይህን ለማየት የግድ ቦታው ላይ መገኘት አለብህ ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን ስትጠቀም የምታመነጨው ታዳሽ ኃይል መሆኑ የምንኖርባትን ምድር ተፈጥሯዊ ምህዳር ለመጠበቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከአፍሪካ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ህዝብ መካከል 600 ሚሊዮኑ የኢነርጂ አቅርቦት እንደማያገኝ ጠቅሰው፥ህዳሴ ግድብ ለዚህ የኃይል ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ዓለም ለአፍሪካውያን የኢነርጂ ፍላጎት አቅርቦት እንዲሟላ የሚያስችል ከበቂ በላይ የፋይናንስ አቅም እንዳለው ጠቅሰው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም