ቀጥታ፡

የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል ጥንታዊነቱን፣ባህሉንና ህዝባዊ መሰረቱን ይዞ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል

አዲስ አበባ፤ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡- የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል ጥንታዊነቱን፣ ባህሉንና ህዝባዊ መሰረቱን ይዞ በደመቀ ሁኔታ ነገ እንደሚከበር የአዊ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ገልጸዋል።

በአማራ ክልል አዊ ዞን "ፈረስን ለባህል ትራክተርን ለእርሻ" በሚል እሳቤ የታሪክ እጥፋት የሚፈጥር ሥራ መጀመሩንም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ገልጸዋል።


 

86ኛው የአገው ፈረሰኞች ማህበር "የአብሮነት ቅርስ፣ የሰላም ውርስ" በሚል መሪ ሀሳብ በዓል ነገ በእንጅባራ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በድሞቀት ይከበራል።

የበዓሉ አካል የሆኑ ከ30 በላይ ትራክተሮች ለዕይታ የቀረቡበት የትራክተር ኤግዚቢሽንና የባህል ትዕይንቶች ዛሬ በእንጅባራ ከተማ በመካሄድ ላይ ናቸው።

የአዊ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው፥ የአንጋፋው የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ መምጣቱን ገልጸዋል።


 

በዓሉ ታሪክና ባህልን ከዘመናዊነት በዋጀ መልኩ በመከበር ላይ መሆኑን ጠቅሰው፥ የዘንድሮ በዓል በበርካታ የገጠርና የከተማ የልማት ኢኒሼቲቮች የታጀበ መሆኑን ተናግረዋል።

ፈረስና የአገው ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው በማንሳት፥ ፈረስ ለአገው ህዝብ አርሶ፣ ወቅቶ፣ ምርቱን ወደ ጎተራ አስገብቶ፣ በደስታና በሀዘኑ አጅቦ ክብርና ኩራቱን የሚገልጽበት ባለውለታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ በዞኑ ፈረስን ለክብርና ለባህል እርሻን በትራክተር በሚል እሳቤ የፈረስን የእርሻ አገልግሎት በዘመናዊ ትራክተር ለመተካት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ታሪካዊ እጥፋት የሚፈጥር ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በዛሬው የትራክተሮች ኤግዚቢሽንም ወደ ዘመናዊ ግብርና የመሻገር ጉዟችንን አሳይተንበታል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፥ ለዘንድሮ የበጋ እርሻ በርካታ ትራክተሮች መግባታቸውን ጠቅሰዋል።ከ100 በላይ ትራክተሮች የግዥ ሂደት ላይ ናቸው ብለዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አያይዘውም የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል ጥንታዊነቱን፣ ባህሉንና ህዝባዊ መሰረቱን ይዞ በደመቀ ሁኔታ ነገ እንደሚከበር ገልጸዋል።

በበዓሉ ላይ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የዞኑ ህዝብና በርካታ ጎብኝዎችን ጨምሮ ከ100 ሺህ ያላነሰ ህዝብ እንደሚታደም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም