7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው
አዳማ ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡- 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ማህበር ገለፀ።
ማህበሩ በምርጫ ስነ ምግባር ላይ ለክልሉ ወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በአዳማ እየሰጠ ይገኛል።
የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወጣት አህመድኑር አሊይ በስልጠናው ላይ እንዳለው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማህበሩ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል ።
ማህበሩ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በታዛቢነትና የወጣቶችን ግንዛቤ በማሳደግ በመሳተፍ ምርጫው ውጤታማ እንዲሆን መስራቱን አስታውሷል።
ከዚህ በመነሳትም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰራን ነው ብሏል።
ማህበሩ ለአባላቱ የምርጫ ስነ ምግባርን በተመለከተ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው የዛሬው መድረክ የዚሁ አካል መሆኑን አመልክቷል።
የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ ሮዛ ቢያ እንደገለፁት፤ የሲቪል ተቋማት ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገባት የጎላ ሚና አላቸው።
በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ማህበር ይበልጥ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ማህበሩ ለአባላቱ የምርጫ ስነ ምግባርና ከምርጫ ጋር በተያያዙ ህጎች ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
ከስልጠና ተሳታፊዎች መካከል ከምዕራብ ሸዋ ዞን የመጣው ወጣት ሂርጳሳ ገላልቻ በበኩሉ፤ ስልጠናው የወጣቶችን የምርጫ ተሳትፎና ውጤታማነት ድርሻን የሚያሳድግ መሆኑን ጠቅሷል።
ወጣቱ በህገ መንግሥቱ የተሰጠውን መብት በመጠቀም መምረጥና መመረጥ እንዲችልም ግንዛቤ የፈጠረ መልካም አጋጣሚ ነው ብሏል።
በተለይ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ እንዲዳብር የወጣቶች ተሳትፎና ሚና የጎላ መሆኑን የተረዳንበት ነው ያለው ወጣቱ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የድርሻውን እንደሚወጣም አክሏል ።
የአርሲ ዞን ወጣቶች ማህበር አባል አሚና አብደላ በበኩሏ፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን ከወጣቶች ብዙ እንደሚጠበቅ መረዳቷን ገልጻለች ።
ለዚህም ሌሎችን በማስተማርና የራሷን ሚና ለማጠናከር መዘጋጀቷን ተናግራለች ።