ቀጥታ፡

15ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡-የሀገር ውስጥ ምርቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስርን ለማጠናከር ያለመው 15ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ ከጥር 27 እስከ የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል ዐደባባይ እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ በንግድ ትርዒቱ ላይ ከ300 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በሚካሄደው የንግድ ትርኢት ላይ ከ20 በላይ ሀገራት የሚመጡ ሃምሳ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል።

ዝግጅቱ ምርትን ከማስተዋወቅ ባለፈ በተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሳለጥ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል።

በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሊቁ በነበሩ በመግለጫቸው እንዳሉት ኤግዚቢሽኑ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያበረታታል።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየጣረች ባለችበት በዚህ ወቅት እንደዚህ ያሉ መድረኮች ለሀገሪቱ ምርቶች መተዋወቅና ለገጽታ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አስረድተዋል።

በተጨማሪም የንግድ ትርዒቱ የሀገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ በማነቃቃትና አዳዲስ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም