ቀጥታ፡

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡-በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኢትዮጵያዊያን ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር በማስተላለፍ ዳግማዊ የዓድዋ ድልን የሚጎናጸፉበት ወሳኝ ዕድል መሆኑን በዩናይትድ ኪንግደም የበርኒንግሃም የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በክልሎች፣ በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዜጎች አጀንዳ የማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር ምዕራፎችን ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል።


 

በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዜጎች በደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ በስዊዲንና በእንግሊዝ በተዘጋጀ መድረክ ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ምክክር አካሂደዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ አሉኝ የሚሏቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ በማስረከብ ተወካዮቻቸውን መርጠዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች በሀገራቸው ልማት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ገንቢ ሚና እየተወጡ ነው።


 

በተለያዩ ክፍለ ዓለማት በተካሄደው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ መድረክ ስኬታማነት የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት አዎንታዊ ሚና መወጣታቸውን ገልጸዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረኮቹም በዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችንና ተሳታፊዎችን በመለየት ለኮሚሽኑ ማቅረባቸውን ተናግረዋል::

በዩናይትድ ኪንግደም የበርኒንግሃም የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ ምክትል ሊቀመንበር ሄለን በፍቃዱ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክር በታሪክ አጋጣሚ የሚገኝ ወሳኝ ዕድል ነው ብለዋል።


 

የተለያዩ ሀገራትም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያጋጠማቸውን የፖለቲካ ቅራኔ በሀገራዊ ምክክር እልባት በመስጠት ዕድገትን የሚያፋጥን ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት እንደቻሉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም በብዝኅ ማንነት ያሸበረቁ የአንድነት ጌጦችን ለዘላቂ ሀገረ መንግስት ግንባታ ለማዋል በሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባት ማጽናት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም በተካሄደው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ ለሀገር የሚበጁ ወሳኝ ሃሳቦች እንደተንጸባረቁበት አስታውሰዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረኩም ለኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የሚበጁ ሃሳቦችን በማዋጣት የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።


 

ሀገራዊ ምክክሩም ኢትዮጵያዊያን አለመግባባቶችን በሰለጠነ የምክክር መድረክ መፍትሔ በመስጠት ዳግማዊ የዓድዋ ድልን መድገም የሚችሉበት ወሳኝ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያዊያን በታሪክ አጋጣሚ የተገኘውን የሀገራዊ ምክክር ዕድል በሚገባ በመጠቀም ለሀገር አንድነትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም