ቀጥታ፡

ከክልሉ ከ121 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል

አዲስ አበባ ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡-ከኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ121 ሺህ ቶን በላይ ጥራት ያለው ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የቡና ሻይና ቅማማ ቅመም ግብይት ዳይሬክተር አቶ አዳሙ በንቲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቡናን በጥራትና በብዛት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።


 

የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳለጥም ህገወጥ የቡና ግብይትን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ግብረ ሀይል ተዋቅሮ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመትም 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቶን ቀይና ጀንፈል ቡናን ለመግዛት ታቅዶ ባለፉት ስድስት ወራት ከ600 ሺህ ቶን በላይ ቡና ከአምራቾቹ መገዛቱን ተናግረዋል። 

ከቡና አምራቾች በግዥ የቀረበውን ቡና በፋብሪካዎች አማካኝነት አቀነባብሮ ለገበያ ዝግጁ የማድረግ ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል። 

ከተገዛው ቡና ውስጥ 121 ሺህ 107 ቶን የታጠበና የተቀሸረ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን አስታውቀዋል።


 

በክልሉ የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ የቡና ማድረቂያና አልጋ በጥንቃቄ በማዘጋጀት፣ የእርጥበት መለኪያና ሌሎች ሙያዊ ድጋፎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ የቡና ጥራት መለኪያ ማዕከላት በጅማ፣ በኢሉአባቦር፣ በቡኖ በደሌ፣ በቄለም ወለጋና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በምዕራብ ጉጂ ዞኖች በባለሀብቶች መከፈታቸውን ተናግረዋል።


 

የማዕከላቱ ወደ ስራ መግባት ወጪና ጊዜን ለመቀነስ እንዲሁም የምርቱን ደረጃ ለማወቅ ከማስቻል ባለፈ አጠቃላይ ጥራቱን ለመጠበቅ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ዘርፉን በማበረታታት በቡና ልማት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም