የክልሉን የቱሪዝም ጸጋዎች በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን የቱሪዝም ጸጋዎች በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ባቢሌ ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ያሉ እምቅ የቱሪዝም ጸጋዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምቢሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ቱሪዝም ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየሰራችባቸው ካሉ አምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
ይህንን መነሻ በማድረግ በክልሉ የኢኮ ቱሪዝምና የቱሪዝም መዳረሻዎችን የመለየት፣ የማልማት፣ የማስተዋወቅ እንዲሁም ወደ ኢኮኖሚ ጠቀሜታ የመቀየር ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
በክልሉ እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል የምስራቅ ሐረርጌ ዞንና ማያ ከተማ ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።
በአካባቢው ካሉ የቱሪዝም ጸጋዎች መካከል የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ፣ ትክል ድንጋዮች፣ ዋሻዎችና የማዕድን ውጤቶችን ጠቅሰው፣ እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ ለማስተዋወቅ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች መሟላታቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ ያለውን የቱሪዝም ሀብት ለማልማት ከመንግስት ባለፈ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ነው ሃላፊዋ ያነሱት።
ከዚህ አኳያ የግል ዘርፉ በአካባቢው ያለውን እምቅ ጸጋ በማልማት ለቱሪዝም ዘርፉ ዕድገት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሚስኪ መሀመድ በበኩላቸው፣ ዞኑ በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች እንዳሉትና ይህን ሀብት የማልማት፣የመንከባከብና የማስተዋወቅ ሥራ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
''በአንድ ወረዳ አንድ የቱሪዝም ማዕከል'' በሚል የየአካባቢውን የቱሪዝም ጸጋ ለማልማት የተጀመረው ኢንሼቲቭም ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል።
የባቢሌ ወረዳ ዝሆኖችና ትክል ድንጋዮችን ጨምሮ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች ባለቤት እንዲሁም የማዕድንና የለውዝ ምርት መገኛ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የባቢሌ ከተማ ከንቲባ አህመድነጃሽ አብዱራሃማን ናቸው።
ይህን ሃብት ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማዋል በአግባቡ ለማልማትና ለማስተዋወቅ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች የቱሪዝም መስህቦችን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።።
ጎብኚዎችም በአካበቢው ነዋሪዎች እንግዳ አቀባበልና በተመለከቱት የተፈጥሮ ሀብት መደመማቸውን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ካሉ አምስት የቱሪዝም በሮች መካከል በምሥራቅ በር በኩል ያለውን በምስራቅ ሐረርጌ ዞንና ማያ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።