በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ለሚታደሙ እንግዶች የላቀ አገልግሎት ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ለሚታደሙ እንግዶች የላቀ አገልግሎት ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡- በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ለሚታደሙ እንግዶች የላቀ አገልግሎት ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ አስታወቁ።
ኮሚሽነሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አዲስ አበባ በዓመት ውስጥ እስከ 150 የሚደርሱ ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በስኬት የማስተናገድ ልምድና ዐቅም እንዳላት አንስተዋል።
በዚህም መሠረት 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችም ምቹና ቀልጣፋ የመስተንግዶ አገልግሎት እንዲያገኙ ዝግጅት መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል የመዲናዋ ስኬታማ የልማት ሥራዎች አዲስ አበባን በማስዋብ የከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት በማጽናት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊያና ማኅበራዊ ፋይዳ እያበረከቱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ተሳታፊ እንግዶችም የመዲናዋን የመስኅብ ስፍራዎች የሚጎበኙበትን ዕድል በመፍጠር የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም ከባለድርሻ አካላት ጋር ዝግጅት መደረጉን ነው ያመላከቱት።
ጉባዔው የሀገራት መሪዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ስለሚታደሙ የሀገርን ገጽታ ለዓለም በአግባቡ ለመግለጥ ትልቅ ዕድል መሆኑንም አመላክተዋል።
ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ሆቴልና ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ጋር በመተባበርም ለጉባዔው ታዳሚዎች ኢትዮጵያዊ ዕሴት የተላበሰ የመስተንግዶ አገልግሎት ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን አብራርተዋል።
የሆቴሎችን የአገልግሎት መሠረተ ልማት በማሟላት እንግዶች የተሻለ የቆይታ ጊዜ እንዲኖራቸው ለማስቻል ሙያዊ ምክረ ሐሳቦችን የሚሰጥ የሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ጉባዔው “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሐሳብ ከየካቲት 7 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።