ቀጥታ፡

ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡- በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችል ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት አስታወቁ።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሴ ጥላሁን እንዳሉት፤ በምርጫ ሂደት የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

በዚህም መሠረት በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አካል ጉዳተኞች በምርጫ ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየተሠራ መሆኑን ነው ለኢዜአ የተናገሩት።


 

የአዲስ አበባ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት እናትዓለም እንዳለ፤ በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓትን የሚያጎለብት አደረጃጀት በመፍጠር የሴቶችን የነቃ ተሳትፎ ማረጋገጥ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም ከ2 ሺህ በላይ የማኅበሩ አባላት ለምርጫ ታዛቢነት በመመዝገብ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያቀርቧቸው አማራጭ ሐሳቦችና ሴቶች በሀገራዊ ምርጫው የሚኖራቸውን ገንቢ ሚና የሚያጎለብት ሥልጠና እንደሚመቻች አመላክተዋል።

አክለውም ጊዜው ሲደርስ ሴቶች ይበጀናል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፃቸውን ለመስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መያዝ እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል።


 

የፖለቲካ ፓርቲዎች በፕሮግራሞቻቸው አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ለሚሸፍነው ወጣት የሰው ኃይል ትኩረት እንዲሰጡ ያስገነዘቡት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት በረከት ብርቢርሳ ናቸው።

ማኅበሩም ምርጫው የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጉላት በተለያዩ የትምህርትና ሥልጠና መርሐ-ግብሮች የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ነው ያመላከቱት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ የዝግጅት መርሐ-ግብር ቀርፆ እየሠራ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም