ፋይዳ መታወቂያ ዜጎች ሁሉን አቀፍ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ፋይዳ መታወቂያ ዜጎች ሁሉን አቀፍ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ነው
ገንዳ ውኃ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡-ፋይዳ መታወቂያ ዜጎች ሁሉን አቀፍ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደገለፁት፤ ብሔራዊ መታወቂያው ዜጎች የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ ፋይዳው የጎላ ነው።
በዚህም ዜጎች ሁሉን አቀፍ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ተጠቃሚነታቸው እንደሚረጋግጥም አክለዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቡድን መሪ አቶ ስሜነው ተላከ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎቶችን በማሳለጥ የዜጎችን ፍላጎት የሚያሟላ ነው።
መታወቂያው ዜጎች በየተቋማትና ድርጅቶች የሚፈልጉትን አገልግሎት ለማሳለጥ የሚረዳ ከመሆኑ ባሻገር ደህንነታቸውን በመጠበቅ ስጋት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ተቋማትንና ግለሰቦችን ከአጭበርባሪዎች በመጠበቅ አስተማማኝ የሆነ እንቅስቃሴ እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
የእጅ፣ የፊትና የዓይን አሻራን አካቶ የያዘው መታወቂያው ወንጀልን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈንም ሰፊ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ነው የገለጹት።
በተጨማሪም የአገር ደህንነትን ለመጠበቅ ጭምር ወሳኝ ሚና የሚጫወት የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑንም አስረድተዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን መሬት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስናቀው ተክለማርያም በበኩላቸው፤ ፋይዳ መታወቂያ ለገጠር መሬት አስተዳደር የላቀ ጥቅም እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት።
የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል በመንግስት በኩል የተያዙ ኢንሼቲቮችን ተግባራዊ ለማድረግ የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ አንዱ የማሳለጫ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም የገንዳ ውኃ አገልግሎት ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጋ ተካ በበኩላቸው፤ በየቀኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደንበኞች መታወቂያውን በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህም ህብረተሰቡ መታወቂያው የሚሰጠውን ሰፊ አገልግሎት በሚገባ መገንዘቡን እንደሚያመላክትም አስረድተዋል።
ብሔራዊ መታወቂያው በተቋማትና በተገልጋዩ መካከል መተማመንን በመፍጠር ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲኖር ያደርጋልም ብለዋል።