ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በግማሽ በጀት ዓመቱ 375 ሺህ ነዋሪዎች የንፁህ የመጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ሆነዋል

ነቀምቴ  ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በግማሽ በጀት ዓመቱ 375 ሺህ ነዋሪዎች የንፁህ የመጠጥ ውኃ ተጠቃሚ መሆናቸውን የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ የውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አራርሶ አብዱለጢፍ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቢሮው የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ያሳደጉ ስራዎችን አከናውኗል።

በዚህም በግማሽ በጀት ዓመቱ 375 ሺህ የክልሉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማት ግንባታን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እና በጀት ለማጠናቀቅ በተሰሩ ስራዎች በግማሽ ዓመቱ 670 ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉንም አስረድተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ቢሮው የውኃ ሀብት አስተዳደር ስራዎችን የማጠናከር፣ የሳኒቴሽን እና የኢነርጂ አቅርቦትን የማሳደግ ስራ በትኩረት ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

በሰባት የክልሉ ከተሞች ላይ የፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው የአብዛኞቹ ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በቀጣይም በግንባታ ላይ የሚገኙ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማት ግንባታን ፈጥኖ በማጠናቀቅ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን የማሳደጉ ስራ በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም