የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 17 ጨዋታዎች በስምንቱ አሸንፎ በአራቱ ተሸንፎ በአምስቱ አቻ ወጥቷል። በጨዋታቹ ላይ 18 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
የሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሃዋሳ ከተማ በ29 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ17 ጨዋታዎች መካከል በስድስቱ ድል ሲቀናው ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 11 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 8 ጎሎችን አስተናግዷል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ26 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሃዋሳ ከተማ በ17ኛ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ ከወጣበት ጨዋታ በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል ያልቀናው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ምድረ ገነት ሽሬ ከኢትዮጵያ መድን በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ምድረ ገነት ሽሬ በሊጉ ካከናወናቸው 17 ጨዋታዎች መካከል አምስቱን አሸንፏል። በስድስቱ ጨዋታዎች ሲሸነፍ በተመሳሳይ ስድስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 13 ጎሎች ገብተውበታል።
ኢትዮጵያ መድን 17 ጨዋታዎችን አድርጎ አራት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ሰባት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 12 ግቦችን በ17ቱ ጨዋታዎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 15 ግቦችን አስተናግዷል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በ18 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ምድረ ገነት ሽሬ ከ17ኛ ሳምንት የአቻ ውጤት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ኢትዮጵያ መድን ማሸነፍ ከሶስት ነጥብ ባለፈው ከወራጅ ቀጠና እንዲርቅ ያደርገዋል።
ወላይታ ድቻ ከአዳማ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ወላይታ ድቻ በ15 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። አዳማ ከተማ በ27 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ባለፉት ሰባት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ያላሸነፈው ወላይታ ድቻ ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ነው።
በ17ኛ ሳምንት ከመቀሌ 70 እንደርታ አቻ የተለያየው አዳማ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ ጥር 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ሲዳማ ቡና ሊጉን በ33 ነጥብ ይመራል።
የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በተመሳሳይ ስምንት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ እየመሩ ይገኛል።