የአርባምንጭን የተፈጥሮ ገጸ-በረከቶች አልምቶ ለቱሪስት መስህብ ለማዋል ይበልጥ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአርባምንጭን የተፈጥሮ ገጸ-በረከቶች አልምቶ ለቱሪስት መስህብ ለማዋል ይበልጥ መስራት ይገባል
አርባምንጭ ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- የአርባምንጭን የተፈጥሮ ገጸ-በረከቶችን ጠብቆና አልምቶ ለቱሪስት መስህብ ለማዋል ይበልጥ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ።
የፌደራልና የክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ማምሻውን የአርባምንጭ ከተማ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ደኤታ ስዩም መኮንን እንዳሉት፤ የአርባምንጭ ከተማና አካባቢው ለቱሪስት መስህብ መሰረት የሆኑ አባያና ጫሞ ሀይቆች፣ የደኖችና የምንጮች መገኛ ነው።
የቱሪስት መስህቦቹን በማልማት የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ የተሰሩ ተግባራት መጠናከር እንዳለባቸው አንስተው፤ ከከተማዋ እስከ 40ዎቹ ምንጮች ድረስ የተገነባው 1 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የደረጃ መንገድ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።
አካባቢው ከተፈጥሮ ፀጋዎች ባለፈም የጥበብ ምንጭ በመሆኑ ይህን ይበልጥ በማልማትና በማስተዋወቅ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት ማዋል ይገባል ብለዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አብርሃም አለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአርባምንጭ ከተማና አካባቢው የተፈጥሮ ገጸ-በረከቶችን ጠብቆና አልምቶ ለህዝብ ጥቅም ለማዋል የሚደረገው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
የአርባምንጭ አካባቢን እምቅ የመስህብ ስፍራዎች ማልማት ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በአርባምንጭ ከተማና ዙሪያው ያሉ የመስህብ ስፍራዎችን በመመልከታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ የሶማሌ ክልል አካባቢ ጥበቃና ገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አቶ ሂላል መሐመድ ናቸው።
የመስህብ ስፍራዎችን ወደ ሀብት ለመቀየር የሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ የማንሠራራት ጉዞ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
በአካባቢው ያሉ ገጸ-በረከቶችን ማልማት የቱሪዝም ኢኮኖሚን ከመገንባት ባለፈ ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።
የመንግስት የስራ ሃላፊዎቹ የጋሞ ልማት ማህበር 40/42 የደረጃ መንገድ ፣40 ዎቹ ምንጮች፣ የአርባምንጭ ደኖችንና በዙሪያው ያሉ የአባያና ጫሞ ሀይቆችን ገጽታና ሌሎች ልማቶችን ተመልክተዋል።