የሀረሪ ክልል ካቢኔ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ አልሚዎች የመስሪያ ቦታ በምደባ እንዲሰጥ ውሳኔ አስተላለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የሀረሪ ክልል ካቢኔ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ አልሚዎች የመስሪያ ቦታ በምደባ እንዲሰጥ ውሳኔ አስተላለፈ
አዲስ አበባ፤ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡-የሀረሪ ክልል ካቢኔ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ አልሚዎች የመስሪያ ቦታ በምደባ እንዲሰጥ ውሳኔ አስተላፏል።
የሀረሪ ክልል መስተዳደር ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ አልሚዎች በክልሉ እንዲያለሙ የመስሪያ ቦታ በምደባ እንዲሰጥ ውሳኔ አስተላልፏል።
የመስሪያ ቦታ እንዲሰጥ ውሳኔ የተላለፈውም በልዩ ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው በተለይ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በአግሮ ኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪን፣በቅይጥ አገልግሎትና በጋራ የመኖሪያ ቤት አፓርትመንት እንዲሁም ለመዝናኛ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ነው።
መስተዳድር ምክር ቤቱም በአጀንዳው ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።
የክልሉ መንግስት በክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፉን የበለጠ ለማነቃቃት በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል።
በቀጣይም ፋይዳ ባላቸውና የህዝብን ተጠቃሚነት በሚያጎለብቱ ዘርፎች ላይ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።