የስፖርት ውድድር እና ፌስቲቫሉ አብሮነትና ወዳጅነትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ውድድር እና ፌስቲቫሉ አብሮነትና ወዳጅነትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል
ጅማ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡-በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል የሚካሔደው የስፖርት ውድድር እና ፌስቲቫል አብሮነትና ወዳጅነትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑ ተመላከተ።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች እየተካሄደ ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ውድድር እንደቀጠለ ነው።
በሀገሪቱ ያሉ 49 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ልኡካን ቡድኖቻቸውን ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ ልከው ደማቅ የመክፈቻ መርሃግብር ተካሄዶ ውድድሩ እንደቀጠለ ነው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የስፖርታዊ ውድድሩ እና ፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች እንዳሉት፤ ፌስቲቫሉ መካሔዱ ከስፖርታዊ ውድድሩ ባሻገር አብሮነትና ወዳጅነትን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው።
ውድድሩ ለመቀራረብና ወዳጅነትን ለማጠናከር ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጎን ለጎን የተለያዩ አካባቢዎች ባሕል፣ ታሪክና እሴትን ለማወቅ እንደሚረዳም ነው የተናገሩት።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የመጣው ሮት ቻውል ዶያክ፤ ስፖርታዊ ውድድሩ አብሮነትንና አንድነትን የሚያጠናክር በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል።
ከተለያዩ የሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ተማሪዎች ውድድሩን ለማካሔድ በአንድ ቦታ መገናኘታቸው እርስ በእርስ ለመተዋወቅ፣ ለመግባባትና አካባቢዎችን ለማወቅ ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑንም አመላክቷል።
በዩኒቨርሲቲው መገኘታችን የጅማ ከተማን እና ታሪካዊ ቦታዎቿን ለመጎብኘት፣ የአካባቢውን ባህልና ታሪክ ለማወቅ አስችሎናል ያለው ደግሞ ከመቅደላ አንባ ዩኒቨርሲቲ በውድድሩ ላይ የተሳተፈው ናትናኤል ደምሌ ነው።
ስፖርት ፌስቲቫሉ ሀገርን በተሻለ መንገድ ለማወቅ፣ አንድነትን ለማጠናከር፣ ወዳጅነትን ለማጎልበት የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ነው ያነሳው።
ውድድሩ ወጣት ስፖርተኞችን ለማፍራት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ደግሞ ከሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የመጡትና የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ኤልሳቤጥ ብርሃኑ ናቸው።
ኹነቱ ከስፖርታዊ ውድድር ባለፈ እርስበርስ ይበልጥ ለመተዋወቅ እና አብሮነትን ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን አብደታ ፈይሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀውን የስፖርት ውድድር እና ፈስቲቫል ለመታደም ቡድኑን እየመሩ መምጣታቸውን ገልጸው በዚህም ጥሩ ቆይታ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
መርሃ-ግብሩ ተማሪዎች ሀገራቸውን እንዲያውቁ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን እንዲያዳብሩ እና ታሪካዊ ስፍራዎችንም እንዲጎበኙና እንዲያውቁ ለማድረግ ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።