ቀጥታ፡

በከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር  የተጠቃሚዎችን የስራ ተነሳሽነት ማሳደግ ተችሏል

ሰመራ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት  መርሃ ግብር  የተጠቃሚዎችን የስራ ተነሳሽነት እያሳደገው መሆኑን  የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።

በሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር  በከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር የታቀፉ ዜጎች  ሀብት አፍርተው ወደ ሌላ  ምእራፍ በዛሬው ዕለት ተሸጋግረዋል።

በዚህ ወቅት በቢሮው የከተሞች ምግብ ዋስትና ዳይሬክተር ከድር መሐመድ እንዳሉት፤ መርሃ ግብሩ የዜጎችን የልማት ተሳትፎና  ተጠቃሚነት ማሳደግ አስችሏል።


 

በመርሃግብሩ የተሳተፉ ዜጎች  የከተሞችን ውበትና ፅዳት ከመጠበቅ ባለፈ በተሰማሩበት ስራ ገቢያቸውን አሳድገው ጥሪት በመቋጠር ወደ ሌላ ስራ መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በሚገኙ ሰመራ ሎጊያ፣ አበአላና አይሳኢታ ከተሞች የተተገበረው የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃግብር የስራ ባህልን በማሳደግ፣ የከተሞች ውበት መጠበቅና የጎርፍ መከላከል ስራዎች ላይ ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።

የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት  መርሃ ግብር  የተጠቃሚዎችን የስራ ተነሳሽነት እያሳደገው  መሆኑንም  አስታውቀዋል።

በሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የከተማ አገልግሎትና አቅርቦት ፅህፈት ቤት የሴፍቲኔት ዳይሬክተር አቶ አህመድ ዋሬ በበኩላቸው፤ በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ  ዜጎች ከእለት ገቢያቸው አልፈው በቆጠቡት ገንዘብና በመንግስት ድጋፍ ወደ ቀጣይ ምእራፍ መሸጋገራቸውን አንስተዋል።


 

በከተማው በዚሁ መርሃግብር ባለፈው ዓመት 168 ሰዎች መመረቃቸውን አስታውሰው፤ በአሁኑ ዙርም 43 ሰዎች  ገቢያቸውን በማሳደግ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገራቸውን  ተናግረዋል።

ዛሬ ከተመረቁት የመርሃግብሩ ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ ፋጡማ ሀሰን በሰጡት አስተያየት፤በመርሃ ግብሩ ታቅፈው በተሰማሩበት የከተማ  ጽዳት  ቤተሰቦቻቸውን ከማስተዳደር አልፈው ሀብት አፍርተው ወደ ቀጣይ ምእራፍ መሸጋገራቸውን አንስተዋል።


 

ከልማታዊ ሴፍቲኔት ወደ ፍየሎች ማድለብ ስራ  መሸጋገራቸውን  የገለፁት ደግሞ የሠመራ ከተማ ነዋሪዎቹ አቶ ኖራ ዓሊ እና ኮሎይታ ሀሰን ናቸው።


 

የልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር  የስራ ባህላቸውን  በመለወጡ ስራቸውን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል።


 

መርሃ ግብሩ በክልሉ ላለፉት አመታት 18 ሺህ 203  የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ ወደ ቀጣይ ምእራፍ ማሸጋገር መቻሉን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም