የሀገራዊ ምክክር ስኬታማ ምዕራፎችን በዲጂታል ሥርዓት በመሰነድ ለጥናትና ምርምር ግብዓት ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራዊ ምክክር ስኬታማ ምዕራፎችን በዲጂታል ሥርዓት በመሰነድ ለጥናትና ምርምር ግብዓት ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የሚያልፍባቸውን ስኬታማ ምዕራፎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት በመሰነድ ለቀጣይ ጥናትና ምርምር ግብዓት ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።
በምክክር ሂደት ያለፉ ሀገራት የውስጥ ችግሮቻቸውን እልባት በመስጠት በዜጎቻቸው መካከል ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ችለዋል።
ኢትዮጵያም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋም እንደ ሀገር በማያግባቡ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት በወሳኝ የምክክር ምዕራፍ እያለፈች ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ስኬታማ የምክክር መድረኮችን በማካሄድ ዋናውን ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለማካሄድ ወሳኝ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ተደርሷል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጄ እንግዳ (ዶ/ር)፤ እንደ ሀገር ለተፈጠሩ ቅራኔዎች እልባት ለመስጠት ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም በዜጎች መካከል በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ የፖለቲካ ቅራኔና አለመግባባቶችን መፍትሔ በመስጠት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱም በኢትዮጵያዊያን የነቃ ተሳትፎ አሳታፊና ገለልተኝነቱን ጠብቆ የተሻለ ውጤት ለማምጣት በወሳኝ የስኬት ምዕራፍ እየተጓዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በሀገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ሙያዊ ምልከታቸውን በማጋራትና ሃሳባቸውን በማዋጣት ገንቢ ሚና እየተወጡ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሙያተኞችም በጥናትና ምርምር እንዲሁም ሌሎች የምክክር ሂደቶች ላይ ህዝብን በማንቃት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የሚያልፍባቸውን ስኬታማ ምዕራፎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት በመሰነድ ለቀጣይ ጥናትና ምርምር ግብዓት ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይ የምክክር ምዕራፍም በዲጂታል ሥርዓት የታገዘ መረጃን መሰነድ የሚያስችል ድጋፍ ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ተማሪዎችም በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ሃሳባቸውን በነፃነት የሚያንሸራሽሩበት ዝግጅቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በተለያዩ ክበባት በማደራጀት በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የሚደርጉት ምክክር ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል ግንዛቤያቸውን በማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።