ኢትዮ-ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት 85 ቢሊዮን ብር ገቢ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ-ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት 85 ቢሊዮን ብር ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮ-ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት 85 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።
በስድስት ወራቱ 1 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብ ግብይት በቴሌብር መፈፀሙንም አስታውቀዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የተቋሙን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት የዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ የሚያረጋግጡ ውጤታማ ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ ተደራሽነትና በዲጂታል አካታችነት ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸው፤ የደንበኞች ቁጥር 87 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቀዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ስትራቴጂክ ዕቅድ አካታችነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይም በገጠርና በታዳጊ አካባቢዎች ላይ የሚደረገው የማስፋፊያ ሥራ ዜጎች በዲጂታል ኢኮኖሚው ውስጥ እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ የታለመ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህ የ6 ወራት አፈጻጸም ተቋሙ በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ ያለውን መሪነት የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል።
በስድስት ወራት ውስጥ የ4ጂ ኔትዎርክ አገልግሎትን ለተጨማሪ 133 ከተሞች ተደራሽ ማድረጉን ተናግረው አጠቃላይ 1 ሺህ 69 ከተሞች የ4ጂ ኔትዎርክ አገልግሎት ተደራሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ተቋሙ የኔትወርክ ጥራትንና ሽፋን ለማሳደግ ባከናወናቸው ተግባራት 278 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱንም ተናግረዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 130 የሚሆኑት በገጠር አካባቢዎች የተገነቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።
በዚህም 102 ወረዳዎች እና 332 ቀበሌዎች አዲስ የኮኔክቲቪቲ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ነው ያሉት።
ይህም ተቋሙ ገጠራማውን የሀገሪቱ ክፍል ከቴክኖሎጂ ጋር ለማገናኘት የያዘውን ግብ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የኢንተርኔት ፍጥነትንና ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችለው የፋይበር (Backbone Fiber Expansion) የማስፋፊያ ሥራ በስፋት መከናወኑን በመግለጫቸው አብራርተዋል።
የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ እየሰራ ያለው ቴሌብር ባለፉት ስድስት ወራት ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል።
በዚህም የቴሌብር ተጠቃሚዎች ቁጥር 58 ነጥብ 6 ሚሊዮን መድረሱን ተናግረው፤ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 1 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብ ግብይት በቴሌብር መፈፀሙን አስታውቀዋል።
በቴሌብር በኩል 16 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ የሚላክ ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን አስታውቀዋል።
ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት 85 ቢሊየን ብር ገቢ ማገኘቱን አስታውቀው ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 37 በመቶ እድገት እንዳለው ተናግረዋል።