ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የባንኮችን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ውጤታማ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የባንኮችን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ውጤታማ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር አድርጓል
ወልቂጤ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የባንኮችን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ውጤታማ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር ማገዙን የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማዘመንና አስተማማኝ ፋይናንስ ሥርዓትን ለመዘርጋት በማስቻሉ ተሞክሮውን በማስፋት ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መግባታቸውንም ለኢዜአ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበኩር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ፀበሉ ይብጌታ፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ ዜጎች ደኅንነታቸው የተጠበቁ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ባሉበት ቦታ ሆነው ገንዘባቸውን ከመቆጠብ ባለፈ ለማንቀሳቀስ እንዲችሉ አድርጓል ብለዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በላቀ ደረጃና ጥራት ለማስቀጠል ያለፉ ስኬቶችን መሠረት በማድረግ ተግባሩን ለማስቀጠል እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
የዳሽን ባንክ ሆሳዕና አካባቢ ሥራ አስኪያጅ መሪሁን መኮንን በበኩላቸው፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ የፋይናንስ ተቋማትን ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ጤናማ የፋይናንስ አሠራር እንዲጠናከር ማድረጉን አስታውቀዋል።
የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገና ከወረቀት ነፃ የሆነ አገልግሎት በመስጠት በርካታ አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ምቹና አስተማማኝ የሆኑ አዳዲስ መተግበሪያዎች እየቀረቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትግበራም የባንኩን አሠራር በተሟላ መንገድ በዲጂታል የታገዘ በማድረግ ተወዳዳሪነቱን ከፍ እንደሚያደርገው አመልክተዋል፡፡
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ የተቋማቸው የአሠራር ሥርዓት እና ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ለውጦች የተገኙበት መሆኑን ያነሱት ደግሞ በእናት ባንክ የሆሳዕና ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ፍፁም ወልዴ ናቸው።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ይፋ መደረግም በተለያየ መንገድ የሚዘዋወርና ለብክነት የሚዳረግ ገንዘብን በመቆጣጠር ረገድ የጎላ ሚና እንደሚያበረክት አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሕግ ባለሙያ የሆኑት መሃሩ ሙጎ፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ የባንኮችን አሠራርና መረጃ አያያዝ በማዘመን የማጭበርበር ወንጀሎችን ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።