በክልሉ ተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ ነው
ባሕር ዳር፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- የተቀናጀ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የተጠናከረ የጤና ሥርዓት ስትራቴጂክ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በክልሉ የጤና አገልግሎት ሥርዓትን ለማዘመን ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
ይህም የጤና ተቋማትን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ የሕክምና መሣሪያዎች እንዲሟሉና ሕብረተሰቡ በቀላሉ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የጤና ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ሥርዓት እንዲዘረጉና አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑ እየተደረገ ያለው ጥረትም ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።
በክልሉ የተቀናጀ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እየተሰጠ ባለው ፈጣን ምላሽ የሕጻናትና የእናቶችን ሞት መቀነስ መቻሉን አመልክተዋል።
የጤና መድኅን አገልግሎትን ለማስፋት በተደረገው ርብርብ በተያዘው ዓመት ሽፋኑን ከ91 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉንም አንስተዋል።
የአምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ የተጠናከረ የጤና ሥርዓት ፕሮጀክት የአማራ ክልል አስተባባሪ አብራራው ታደሰ (ዶ/ር)፤ በክልሉ የጤና ሥርዓቱን ለማዘመን የተጀመሩ ጥረቶች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።
በፕሮጀክቱ የጤና አመራር ዘርፍ የፋይናንስና መረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለማዘመን በጣርማ በር፣ አንፆኪያ ገምዛና ቃሉ ወረዳዎች በሚገኙ 19 ጤና ተቋማት ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደ የሙከራ ትግበራ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን አብራርተዋል።
በቀጣይም ወደ ሌሎች ወረዳዎች አገልግሎቱን የማስፋትና የማዘመን ሥራዎች ለማስቀጠል በቅንጅት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።