ቀጥታ፡

ሪፎርሙ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት የአገልግሎት አሰጣጥን ያዘምናል

አሶሳ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት የአገልግሎት አሰጣጥን ያዘምናል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

የክልሉ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።



 
ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚሁ ጊዜ፤ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል።

የመንግሥት ሠራተኛው የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣትም ዲጂታል ክኅሎቱንና ተወዳዳሪነቱን የሚያሳድግበት ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል የመንግሥት ሠራተኛው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሪፎርሙ ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን በመፍጠር ተወዳደሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ይረዳል ነው ያሉት።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድርና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ጌታሁን አብዲሳ፤ ሪፎርሙ ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እና ወጪ ቆጣቢ የሥራ ስምሪትን ለመተግበር ያግዛል ብለዋል።

በሪፎርሙ ሠራተኞች በሚሰጣቸው ተልዕኮ መሠረት የሚመዘኑበትና ውጤት ተኮር ሥራ መሥራታቸው የሚረጋገጥበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም አመላክተዋል።

የሪፎርም ሥራው በቀጣዩ ዓመት ተጠናቅቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም