ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ማመንጨት እና በቀጣናዊ ኃይል ትስስር ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች ነው - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ማመንጨት እና ቀጣናውን በኃይል በማስተሳሰር ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች እንደምትገኝ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

የልማት አጋሮች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትስስር ያለውን ሚናም አድንቀዋል።

27ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ስብሰባ በሶማሊያ ሞቃዲሾ የተካሄደ ሲሆን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በስብሰባው ተሳትፈዋል።


 

በስብሰባው የኢኒሼቲቩ አባል ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች እና የልማት አጋሮች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

የፋይናንስ ሚኒስትሮቹ ለኃይል ማሰራጫ መሰረተ ልማቶችና ለቀጣናዊ የኢነርጂ ትስስር ስራዎች የፋይናንስ አቅርቦትን በማሳደግ አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ የኢነርጂ አቅርቦትን ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

ከዚህ ቀደም የኢነርጂ ፋይናንስ እና ቀጣናዊ ትስስርን አስመልክቶ በተደረጉ ውይይቶች የነበሩ አጀንዳዎች አፈጻጸምን ገምግመዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የኢነርጂ ትስስር ለቀጣናዊ እድገትና መረጋጋት ያለውን ፋይዳ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2030 ተመጣጣኝ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ የኢነርጂ ተደራሽ የማድረግ ግብ ያለው “National Energy Compact” ኢኒሼቲቭ ትግበራ ከዘጠኝ ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልገውና ከተለያዩ የፋይናንስ አማራጮች የሚገኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ማመንጨትና ቀጣናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስርን በማጠናከር ረገድ ውጤቶች እያስመዘገበች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

በስብሰባው የዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት፣ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ፣ የኮመንዌልዝ እና ልማት ቢሮ እና የጀርመን ኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የልማት አጋሮቹ የዓለም ባንክ እና ሌሎች አጋር አካላት የሚደግፉትና እ.አ.አ በ2030 300 ሚሊየን አፍሪካውያውን አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ የኢነርጂ አቅርቦት እንዲያገኙ የማድረግ ውጥን ባለው “Mission 300” ፕሮግራም ማዕቀፍ አማካኝነት ለኢነርጂ ተደራሽነት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ጋር ካላት የኤሌክትሪክ መስመር ትስስር በተጨማሪ ከሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር ለሚዘረጉ አዳዲስ መስመሮች የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።


 

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትስስር ያለውን አዎንታዊ ሚናም አድንቀዋል።

የፋይናንስ ሚኒስትሮቹ ቀጣናዊ የኢነርጂ ትስስርን የሚያፋጥን የከፍተኛ ደረጃ ኮሚቴ ለማቋቋም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በስብሰባው የኢነርጂ ዘርፍ ለቀጣናዊ ትስስር ያለው ማዕከላዊ ሚና እና የልማት አጋሮች ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ በስብሰባው ከነበራቸው ተሳትፎ በተጨማሪ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ቢሮ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ባዘጋጀችው የእራት ግብዣ ላይ ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ጋር መወያየታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

#Ethiopian_News_Agency

#ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም