ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል 

አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- በሸገር ከተማ የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን የከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ገለጹ።


 

የሸገር ከተማ አሥተዳደር የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ኑሮ በማሻሻል የሕዝብን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ 1 ሺህ የንግድ ሱቆችን በመገንባት ለአርሶ አደሮች አስተላልፏል።

ከንቲባ ተሾመ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የከተማዋን ዘመናዊነት ለማስጠበቅ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የንግድ ሱቆቹም የከተማዋን ገጽታ በማዘመን አርሶ አደሮች ቋሚ የገቢ ምንጭ የሚያገኙበትን ዕድል በመፍጠር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚኖራቸው አመላክተዋል።

ለአርሶ አደሮች የተላለፉ የንግድ ሱቆች የሕዝብን ተጠቃሚነት ወደላቀ ምዕራፍ በማሸጋገር በሥራ ዕድል ፈጠራና ፍትሕዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚያሰፍኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይም የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎችን በማስፋት የአርሶ አደሮችን ኑሮ የማሻሻል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአሥተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ አስተባባሪ ጉግሣ ደጀኔ፤ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት መሠረት በማድረግ የንግድና ኢንቨስትመንት ሽግግርን የሚያሳልጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሱቆቹን ለሌላ ወገን ማስተላለፍ እንደማይቻልም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም