ቀጥታ፡

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን የስራ ጫና በመቀነስና ማህበረሰባዊ እሴትን በማጠናከር በኩል ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2018(ኢዜአ)፦ በኢትየጵያ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን የስራ ጫና በመቀነስና ማህበረሰባዊ እሴትን በማጠናከር በኩል ውጤት እያስገኙ መሆኑን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሌሊሴ ደሳለኝ ገለጹ።  

ፍትሕ ሚኒስቴር ከኢንስቲትዩት ኦፍ ሴኪዩሪቲ ስተዲስ ጋር በመተባበር "ወደ ተመጋጋቢነት፤ በኢትዮጵያ ባህላዊና ዘመናዊ የፍትሕ ስርዓቶችን ማቀናጀት" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የውይይት መድረግ እየተካሄደ ነው።
 
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሌሊሴ ደሳለኝ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት የፍትሕ ስርዓቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ በርካታ የህግ ሪፎርም አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል።
 
በፍትሕ ዘርፉ ከተደረጉ ማሻሻያዎች መካከል ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ውጭ በአማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓት እንዲፈቱ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። 
 
በሪፎርሙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በተቋም ደረጃ መደራጀታቸውን ገልጸው፤ ክርክሮች ከመደበኛው የህግ ስርዓት ውጭ በባህላዊ መንገድ ዕልባት እንዲያገኙ አስችሏል ነው ያሉት።
 
በኢትዮጵያ በተለይም በገጠር አካባቢ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል በባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ፍትህ እንዲሰፍን እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
 
በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ባህላዊ የፍትህ ስርዓት በስፋት ይከናወንባቸዋል ብለዋል።
 
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አስማሚነት በሚልየን የሚቆጠር ገንዘብ ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች ዕልባት ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።
 
ይህም የተከራካሪ ወገኖችን ጊዜና ገንዘብ በመቆጠብ እንዲሁም በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን የስራ ጫና በመቀነስ ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።
 
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ዕርቅ በማውረድና ማህበራዊ መስተጋብርን በመጠገን ዘላቂና ጤናማ የሰዎች ግንኙነት በማጠናከር ትልቅ ውጤት ማምጣታቸውንም ገልጸዋል።
 
በኢትዮጵያ በስምንት ክልሎች ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸው፤ የሚሰጡ ውሳኔዎችን ተግባራዊ የማድረግ አስገዳጅነት እንዲኖራቸው ተደርጓል ብለዋል።
 
የባህላዊ ፍርድ ቤቶች የማቋቋሚያ አዋጅ መውጣቱና ዕውቅና መሰጠቱ ለውጤቱ መሰረት መጣሉን በማንሳት፤ ሁሉም ክልሎች በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
 
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ቀለል ያለ ስርዓት የሚከተሉ፣ ሀገር በቀልና መሰረተ ማህበረሰብ በመሆናቸው በተከራካሪ ወገኖች መካከል ዘላቂ ግንኙነትን ያስቀጥላሉ ብለዋል።
 
የፍትሕ ስርዓቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ የባህላዊና መደበኛ ፍርድ ቤቶችን አቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
 
የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን አቅም ለማሳደግ የማስቻያ ቦታዎችን ማዘጋጀትና ውሳኔዎችን ማስፈጸም ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም