ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች ነው
አርባምንጭ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ተግዳሮት ለሆነው አየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች መሆኗን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስገነዘበ።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ዘርፍና የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ ስዩም መኮንን በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ በትኩረት እየሠራች ነው ብለዋል።
ዓለምአቀፍ ተግዳሮት ለሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠትም ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች መሆኗን አስገንዝበዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርን ጨምሮ በሀገር በቀል ስልቶች ለአየር ንብረት ለውጥ እየተሰጠ ባለው ምላሽም ተጨባጭ ውጤት መምጣቱን አረጋግጠዋል።
የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ እንዳሉት፤ ዜጎች ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብታቸውን ለማረጋገጥ የጽዱና አረንጓዴ ልማት ሥራዎች ተሠርተዋል።
የከተሞች ኮሪደር ልማትን ጨምሮ የጽዱ ኢትዮጵያ፣ የወንዝ ዳርቻና የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቮች ለውጤቱ መገኘት ጉልህ ድርሻ አንዳላቸው አመልክተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የአካባቢ ቁጥጥር ሥርዓትን ለማጠናከር የወጡ ሕጎችና መመሪያዎች ተፈጻሚነት ላይ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራታቸውንም አንስተዋል።
በዚህም የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ በአካባቢ ማኅበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲሁም በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ላይ የተሻለ ውጤት መምጣቱን አንስተዋል።