ቀጥታ፡

በመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎች ከሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች ራስን እንዴት መጠበቅ ይቻላል?

የበርካታ ዜጎች የዕለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴና ግንኙነት ከዲጂታል ሥርዓት ጋር በጥብቅ መተሳሰሩን ተከትሎ፣ በማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ላይ የሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶችና መጭበርበሮች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ ይገኛሉ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተቀናጀ የሳይበር መከላከል አገልግሎት ዲቪዠን ኃላፊ አቤል ተመስገን፤ የዲጂታል መተግበሪያዎች አጠቃቀም ላይ በቂ ንቃተ ህሊና አለመኖር በግለሰቦችና በተቋማት ላይ የከፋ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎትና መሰል የቴክኖሎጂ ምጥቀቶች ጥቃቱን "ኢ-ተገማች" እና ድንበር ተሻጋሪ አድርገውታል።

የተጠቃሚዎች የደህንነት ንቃተ ህሊና ማነስ ደግሞ የተጋላጭነት ምጣኔውን ይበልጥ አስፍቶታል።

በዚህም ምክንያት በቴሌግራም፣ ዋትስአፕ እና መሰል መተግበሪያዎች የግል አካውንቶች የመጠለፍ፣ ሚስጥራዊ መረጃዎች የመመንተፍ እንዲሁም የማጭበርበር ሰለባ የመሆን አደጋዎች በስፋት እየተስተዋሉ ነው።

ተጠቃሚዎች ከመሰል ስጋቶች ራሳቸውን ለመጠበቅ የደህንነት ማስጠበቂያ ስልቶችን በአግባቡ ማወቅና መተግበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ለዚህም የሚከተሉትን ነጥቦች እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በቀላሉ የማይገመት የይለፍ ቃል መጠቀም፣ ባለሁለት ደረጃ ማረጋገጫ አማራጭ በመጠቀም የአካውንት ደህንነትን ማስጠበቅ፣ የግልና የቢዝነስ አካውንቶችን ለይቶ መጠቀም እንዲሁም የመተግበሪያዎችን የደህንነት ማሻሻያ በወቅቱ መጫንን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ አፍሪካ ህብረት ጉባዔ ያሉ ትልልቅ ሁነቶችን እንደ ዕድል በመጠቀም የሚላኩ አሳሳች ሊንኮችና መልዕክቶች እንደሚበራከቱ ገልጸው፤ ማንኛውንም ሊንክ ከመክፈት በፊት በተጠራጣሪነት መመልከትና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ የሁልጊዜ ልምድ ሊሆን እንደሚገባ መክረዋል።

የሳይበር ጥቃት ሰለባ መሆን የግል ጉዳት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ላይም የሰንሰለት ጉዳት እንደሚያስከትልና "እኔን ማን ይጠልፈኛል?" የሚል መዘናጋት ዋጋ እንደሚያስከፍልም አቶ አቤል አስጠንቅቀዋል።

አካውንቱ የተጠለፈበት ሰው በፍጥነት በሌሎች አማራጮች ለአካባቢው ሰዎች ማሳወቅ ያለበት ሲሆን፣ መልዕክት የሚደርሳቸው ሰዎችም የገንዘብ ጥያቄም ሆነ ሌላ መረጃ ሲጠየቁ መጠራጠር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

አንዴ ከተጠለፉ በኋላ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን ለማስመለስ የሚወስደው ጊዜ ውስብስብ በመሆኑ ቅድመ ጥንቃቄው ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል።

ማንኛውም የሳይበር ጥቃት ሙከራ ሲያጋጥም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ነፃ የጥሪ መስመር 933 ላይ በመደወል ወይም በኢሜል ሪፖርት ማድረግ እንደሚቻል ተገልጿል።

#Ethiopian_News_Agency

#ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም